አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ AMU-IUC ፕሮጀክት አማካኝነት በምዕራብ አባያ ወረዳ፣ ላዮ ተርጋ ቀበሌ በሚገኘው የቦሮቦር ማገገሚያ ሰርቶ ማሳያ ስፍራ ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል። በሰርቶ ማሳያ ጣቢያው የቦሮቦር (Gully) መልሶ እንዲገግም ለማድረግ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና ወደ አባያ ሐይቅ የሚሄደውን የደለል አፈር ክምችት ለመቀነስ የሚያስችሉ የድንጋይ እርከኖች (stone check dams) እና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎች በተግባር እየተተገበሩ ይገኛሉ። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በመስክ ምልከታ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የፕሮጀክት ተወካዮች፣ የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርሶ አደሮች እና ዓለም አቀፍ አጋሮች የተገኙ ሲሆን፣ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን በመገምገም በቀጣይ በሰፊው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት / ተክሉ ወጋየሁ፣ በንኡስ ፕሮጀክት 4 ሥር የተከናወኑት ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸው የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል በዩኒቨርሲቲው እና በአርሶ አደሩ መካከል ያለው ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ የተጎዳ መሬት መልሶ ማገገም ሥራ ላይ የተገኙ ዕውቀቶችና ልምዶች ከፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በኋላም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል። በተጨማሪም የተሳኩ ተሞክሮዎችን ማስፋፋት የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት / ተክሉ የመሬት ይዞታ እጥረት እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የመሬት ማገገሚያ ሥራዎችን ከመሥራት ባሻገር የአግሮ ፎረስትሪ ሥራዎችን ማስፋፋት እንዲሁም እንደ እንስሳት እርባታ፣ ዶሮ ማርባት፣ ንብ ማነብ እና ሽመና ያሉ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ አማራጮች ጋር አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

AMU-IUC ፕሮጀክት ማኔጀር / ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የዶክተሬት (PhD) ምርምር ሥራዎችን ከኅብረተሰቡ እውነተኛ ችግሮች ጋር አጣምሮ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ንኡስ ፕሮጀክት 4 ሳይንሳዊ ዕውቀትን፣ የአካባቢውን ባህላዊ ዕውቀትና ቁሳቁሶች በማጣመር የመሬት መሸርሸርን ለመቀልበስ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አብራርተዋል። የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአርሶ አደሮች ቁርጠኝነትና ትክክለኛ መረጃዎች ለሥራው መሠረት መሆናቸውንና ተግባራቱን ዘላቂ ለማድረግ ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ተመራማሪ እና የቦሮቦር ማገገሚያ ሥራዎች አስተባባሪ / ልዑልሰገድ በላይነህ የጫሞና አባያ ሐይቆች ተፋሰስ መካከል በሆኑት በሻፌ፣ ባሶ፣ ሲሌ እና ኤልጎ ተፋሰሶች ውስጥ 1,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ የሳተላይት ምስሎችን፣ የመስክ ቅኝቶችን እና የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተካሄደው ምርምር ለአፈር መሸርሸር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ 7,336 ቦሮቦሮች እና 410 የመሬት መንሸራተቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከተመዘገቡት የቦሮቦር መሸርሸሮች መካከል አብዛኞቹ ወደ አባያ ሐይቅ በሚፈሰው የሻፌ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ለዚህ አካባቢ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። በእነዚህ ተፋሰሶች ላይ የሚታዩ ቦሮቦር መሬቶችን መልሶ ማልማት እርሻዎችንና ማኅበረሰቡን ከጉዳት ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ወደ አባያ ሐይቅ የሚሄደውን የደለል አፈር ክምችት ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በላዮ ተርጋ ላይ የተሰራው ሰርቶ ማሳያ በአካባቢው በሚገኙ ቁሳቁሶች 18 የድንጋይ እርከኖች (stone check dams) መገንባታቸውንና በድሮን በተደረገ ክትትል የቦሮቦር መሸርሸርን በመቀነስ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን / ልዑልሰገድ ተናግረዋል። በተጨማሪም የሦስት ሌሎች አማራጭ የመሬት መሸርሸር መከላከያ ዘዴዎች ውጤታማነት፣ ወጪና ዘላቂነት እየተፈተሸ ይገኛል። በዚህ ሥራ ላይ 25 ያህል ተጎጂ አርሶ አደሮች በማቀድ፣ በግንባታና በክትትል ሂደት ቀጥታ በመሳተፋቸው ማኅበረሰቡ የሥራው ባለቤት እንዲሆን አድርጎታል።

የፕሮጀክቱ ንኡስ መሪ ፕሮፌሰር ማቲው ላለፉት 10 ዓመታት የሻፌ ተፋሰስን ሲጎበኙ እንደቆዩና የአካባቢውን የመሬት ጉዳት መጠን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ቀደም ሲልም አነስተኛ የሸለቆ መከላከያና የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ AMU-IUC ፕሮጀክት በማሳያ ጣቢያው አማካኝነት እነዚህ ጥረቶች በሰፊው እንዲስፋፉ መደገፉን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ከመስክ ማሳያው በመማር ለአካባቢያቸው የሚስማሙ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ያበረታቱት ፕሮፌሰር ማቲው፣ ቦታው የረጅም ጊዜ የመማሪያና የስልጠና ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ጥሪ አቅርበዋል።

በምዕራብ አባያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወገኔ ወሌሉ የአፈር መሸርሸርና የሸለቆ መፈጠር የአካባቢው ዋና ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ የማሳያ ጣቢያ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተግባራዊ የሸለቆ ማገገሚያ መንገዶችን አይተው ልምዱን ወደ ሌሎች ተጎጂ አካባቢዎች ለማስፋፋት ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

አርሶ አደር ቦጋለ ከበደ በበኩላቸው ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረውን የበረታ የአፈር መሸርሸር አስታውሰው፣ የተከናወኑት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የግብርና ምርታማነት እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ውጤቱን ያዩ አርሶ አደሮች ልምዱን በራሳቸው መሬት ላይ እየተገበሩት እንደሆነም  ጠቁመዋል።

የላዮ ተርጋ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳንኤል ቴሮ የማገገሚያ ሥራዎቹ ለማኅበረሰቡ ግልጽ ጥቅም ማምጣታቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች አሰራሩን እየተቀበሉ ያገገሙ መሬቶችን ለሰብል ልማትና ለእንስሳት መኖነት በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የመስክ ምልከታ ቡድኑ ከሌዮ ተርጋ ማሳያ ጣቢያ በተጨማሪ በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ሥር በሚገኙ 10 ወረዳዎች ውስጥ KfW ፕሮጀክት አማካኝነት የሚተገበሩ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም እንቅስቃሴዎችንም ጎብኝቷል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
 
መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
 
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
 
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት