የዩኒቨርሲቲው ሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል 11ኛውን ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሣምንት ከኅዳር 9/2017 ዓ/ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሦስተኛ ጊዜ በሥልጠና፣ በቢዝነስ ሃሳብ ውድድርና በሌሎች መርሃ ግብሮች ሲያከብር የቆየ ሲሆን ኅዳር 13/2017 ዓ/ም በፓናል ውይይት የመዝጊያ ፕሮግራሙን አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ዓመታት ራስ ገዝ ለመሆን የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ የሴኔት መተዳደሪያ ደንብና ስትራቴጂክ ዕቅዱን ለመከለስ ኮሚቴዎች አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምትንን አስመልክቶ የተዘጋጀው የፓናል ውይይትም ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ ጉዞውን እንዲያሳካና የራሱን ገቢ አመንጭቶ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች የተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተ/ባ ፕሮፌሰር) ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሽፕ ሳምንት የሥራ ፈጠራ ባህልን ለማሳደግ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ፈጣሪ እእምሮን የምናበረታታበት፣ በሥራ ፈጠራ ጉዞ ውስጥ ለሚፈጠሩ ተግዳሮቶች መፍትሔ የምናነሳበት ብሎም ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ተቋማዊ ራስ ገዝ የመሆን ራእይ የምንደግፍበት ነው ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ የመሆን ዕቅድ ለማሳካት አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ኢንተርፕርነር የመሆን የአእምሮ ውቅር ያስፈልገዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ይህም ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ከሌሎች አጋሮች ጋር ለሚደረገው መስተጋብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመርሃ ግብሩ የክብር እንግዳ የሆኑት የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር) ኢንተርፕርነሪያል ዩኒቨርሲቲ እና ራስ ገዝ አስተዳደርን አስመልክቶ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ተቋማት ውስጥ የነበራቸውን የአመራርነት የሕይወት ልምድ እና አሁን ላይ የሚመሩትን ተቋም የራስ ገዝ ጉዞ አብነት አድርገው ቁልፍ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመልእክታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ራስ ገዝ የትምህርት ተቋማት ጠንካራ የምኅንድስና፣ የቢዝነስና የሕግ ትምህርት ክፍሎች እንዳላቸው ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ተመራጭ ሆኖ ጎልቶ የሚወጣበት ጠንካራ የትምህርት መስክ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የስኬታማ ኢንተርፕርነር መገለጫ የሆነውን ትልቅ ግብና ራእይ ማስቀመጥ፣ ሀብትን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እና ስጋቶችን ለይቶ በድፍረት መወጣት ግድ ይላል ብለዋል፡፡ ኢንተርፕርነሪያል ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራዎች በኢንተርፕርነርሽፕ የሚመሩ መሆን እንዳለባቸው እንዲሁም በተቋማት፣ በኮሌጆች፣ በት/ክፍሎችና በፕሮግራሞች መካከል ግልጽና ጠንካራ ትስስር ሊኖር እንደሚገባም ሥራ አስፈጻሚው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የሥራ ፈጠራ ልማትና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ወንድወሰን ጀረኔ (ዶ/ር) እደገለጹት ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም በሥልጠና፣ በቢዝነስ ሃሳብ ማበልጸግ እና የቢዝነስ ሃሳብ ውድድሮችን በማካሄድ ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ ራስ ገዝንትን ለማረጋገጥ ስኬታማ ኢንተርፕርኒያል መሆን ግድ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን በሚዘጋጅበት በአሁኑ ወቅት የራስን ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ነጻ ተቋም ለመሆን የማዕከሉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ዓለም አቀፉን የኢንተርፕርነርሽፕ ሣምንት አስመልክቶ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ እይታና አቅማቸው እንዲዳብር ማዕከሉ በሁሉም ካምፓሶች ለተመረጡ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጠ ሲሆን የቢዝነስ ሃሳብ ላላቸው ተማሪዎች ጥሪ አቅርቦ በሁለት ዙር ማጣሪያ ለፍጻሜ የቀረቡ ስድስት ተማሪዎቸን አወዳድሮ የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት አበርክቷል፡፡
በመዝጊያ መርሃ ግብሩ የተካሄደው የፓናል ውይይት ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የመሆን ራእዩን ማሳካት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሃሳብ በመለዋወጥ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመጋራት እና ለሂደቱ የሚጠቅሙ ግብዓቶችን ለማግኘት የተዘጋጀ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ላደረጉ ተማሪዎች የምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን 1ኛ የወጣው የቢዝነስ ሃሳብ ስምንት ሺህ ብር እና ከ2ኛ እስከ 6ኛ ለወጡት ከአምስት ሺህ እስከ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር እንደየደረጃቸው የማበረታቻ ገንዘብ አግኝተዋል፡፡