አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ‹‹Effects of Active Rifting and Thermal uplift on Climate, Soil, Water and Agriculture in Southern Main Ethiopian Rift: Implementing Strategies for Recovery Improvement›› በሚል ርእስ በሦስቱ ተቋማት በተመደበ 12 ሚሊየን ብር የሚሠራ ግራንድ የትብብር ምርምር ፕሮጀክት ጥር 24/2017 ዓ/ም ይፋ አድርገዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በዕለቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በትብብር ያበለጸጉትን ‹‹GO-TOUR›› የተሰኘ በጋሞና በቀድሞው ደቡብ ኦሞ ዞኖች የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያሳይ ዲጂታል ካርታ ፕላትፎርምና መተግበሪያ/Application/ ርክክብ ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር አዲስ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር ከዚህ ቀደም የነበረውን የሚያሻሽል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር ከዚህ ቀደም የካርታ ሥራዎች ድርጅት ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ ትብብር የነበረ መሆኑን አስታውሰው በዩኒቨርሲቲውና በኢንስቲትዩቱ ትብብር የበለጸገው የGO-TOUR ዲጂታል ካርታ ፕላትፎርምና መተግበሪያ የጋሞ እና ደቡብ ኦሞ ዞን ቱሪዝምን ማሳደግ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይፋ የተደረገው አዲስ የምርምር ፕሮጀክትም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውና በእጀጉ ጠቃሚ መሆኑን ያወሱት ም/ፕሬዝደንቱ እንደ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር ፕሮጀክቱ ውጤታማነት አስፈላጊው ድጋፍ ይደርጋል ብለዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የዕለቱ መርሃ ግብር አዲስ የትብብር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ፤ የተጠናቀቀ የትብብር ፕሮጀክት ማስረከቢያ እንዲሁም የአዲስ ትብብር ፕሮጀክት ጽንሰ ሃሳብ ማበልጸጊያ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተጠናቀቀው የትብብር ፕሮጀክት በጋሞ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች (በቀድሞው) የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ካርታ ሥራና የመተግበሪያ ማበልጸጊያ ፕሮጀክት ሲሆን ይህ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በትብብር የተሠራና የአካባቢውን የቱሪስት ፍሰት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በሀገሪቱ ያሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስከ መለየታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ራስ-ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየተጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ተቋሙ ከአገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት ጋር ትስስር እና ትብብር መፍጠርን በእጅጉ የሚፈልግ በመሆኑ ከሁለቱ ተቋማት ጋር የምናደርገው የትብብር ስምምነትና ፕሮጀክት ለዚህ አንድ መገለጫና ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ በተጠናቀቀው ፕሮጀከትም፣ በአዲስ መልክ በሚጀመረው ግዙፍ ፕሮጀከት ላይ እንዲሁም በቀጣይ ሊሰሩ በታሰቡ ፕሮጀክቶች ጭምር ከዩኒቨርሲቲው ጋር ውጤታማ የትብብር ሥራዎችን እየሰራ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላቸው ጸሐይ በበኩላቸው ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ከሁለት ዓመታት በፊት በጋሞና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የቱሪስት መዳረሻዎችን እና ለቱሪስቶች አስፈላጊ የሆኑ መሠርት ልማቶችን የያዝ ካርታ የማዘጋጀት፤ ይህንኑ ካርታ ገላጭ የሆኑ መረጃዎችን በማካተት በሲስተም የተደገፈ ሥራ ለመስራት ፕሮጀክት ተቀርጾ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በአካባቢዎቹ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ለጎብኚዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በጂኦስፓሻል መረጃ አማካኝነት ዝርዝር ይዘተ እንዲኖረው ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ሥራ ተመሳሳይ የቱሪስት ካርታ ሥራዎችን ለመስራት እንደ ሞዴል የሚያገለግል መሆኑን ያወሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ በሚያሰሩ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ በበኩላቸው በቅርቡ ዩኒቨርሲቲዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈራረሙት የቁልፍ ተግባራት ስምምነት ውስጥ የትብብር ሥራዎችን ማጠናከረ አንዱ እንደመሆኑ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው የትብብር ፕሮጀክት እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያደረግነው የመግባቢያ ስምምነት በዩኒቨርሲቲዎችና በኢንደስትሪዎች መካከል የሚኖርን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ መሰል የትብብር ሥራዎች በየተቋማቱ ያለን የሰው ኃብትና ሌሎች ግብአቶችን በማቀናጀት የሚሰሩ እንደመሆናቸው ፋይዳቸው ከአካባቢ አልፎ አገራዊ እንደሆነም አውስተዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በዕለቱ የቀረበውና በትብብር የበለጸገው የዲጂታል ፕላትፎርም፣ ይፋ የተደረገው ግዙፍ ፕሮጀክትና የቀረቡ ተጨማሪ የምርምር ሃሳቦች እንደ ሀገር ተጽዕኖ መፈጠር የሚችሉና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ በቀጣይም መሰል ሀገርንና ማኅበረሰብን የሚጠቅሙና ሕይወት የሚያሻሽሉ የምርምር ፕሮጀክቶችን ለመሰራት ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ይፋ ከተደረገው የምርምር ፕሮጀክት ተመራማሪዎች መካከል የሆኑት አቶ ታለማ ሞገድ በደቡብ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ላይ እየተከሰተ ያለውን የንቁ ፍንጣቂ (active rifting) እና የሙቀት መጨመር( thermal uplift) በአየር ንብረት፣ አፈር፣ በውሃ ጥራት እና በምርትና ምርታማነት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመመርመር የሚደረግ ጥናት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምርምሩን ለመስራት ማስፈለጉን አመልክተዋል። ጥናቱ በዋናነት ከላይ የተመላከቱ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴዎች በአየር ንብረት፣ በአፈር፣ በውሃ እና በግብርና ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተጽዕኖ በመገምገም ማሻሻያ ስልቶችን ለማቅረብና ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምርምር ፕሮጀክቱ ከሶስቱ ተቋማት የተወጣጡ 19 ተመራማሪዎች የሚሳተፉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና የጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አባል ዶ/ር ብርሃን ገሠሠ <<GO-TOUR >> የተሰኘውን ዲጂታል ፕላትፎርም አስመልክቶ ባቀረቡት አጭር ገለፃ ፕላትፎረሙ በጋሞና በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ 256 ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ዝርዘር መረጃ የያዘ፣ በየስፍራዎቹ የሚገኙ ሆቴሎች፣ ባንኮች፣ አስጎብኚ ድርጅቶንና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትንና መሠረት ልማቶችን መረጃ የያዘ በእጅጉ ጠቃሚ የሆነ ፕላትፎርም መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ፕላትፎርሙ ሌሎች በርካታ መረጃዎችን የያዘ መሆኑንና ሰዎች በቀላሉ በስልካቸው መጠቀም የሚችሉት እንደሆነም ዶ/ር ብርሃን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በዕለቱ ‹‹Unlocking Water Quality, Quantity and Dam Safety Monitoring in Ethiopia Using Altimetry Satellites, InSAR Techniques, Bathometric and Ground Survey Data Integration›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የምርምር ንድፈ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን ሃሳቡን በትብብር ወደ መሬት ለማውረድና በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ከጋሞ ዞን አስተዳደር የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት