የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ዛሬ ሐምሌ 24/2017 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ በሚገኝ ተራራማ ስፍራ እና በዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የአንድ ጀምበር የአረንገዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በመርሐ ግብሩ ለአካባቢው የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የወይባ፣ ወይራና ቀርከሃ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በተመሳሳይ በሁሉም ካምፓሰ የሚገኙ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ተክለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸው መርሐ ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ‹‹700 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር›› የመትከል ንቅናቄን መቀላቀልና ማሳካትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መጠበቅና መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው አካባቢ ጥበቃ የማኀበረሰብ ጉድኝት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዐመታት ለሀገራዊ አረንጓዴ አሻራ ተልእኮ፣ ለከተማ ውበት እንዲሁም ለአትክልትና ፍራፍሬ የሚሆኑ ችግኞች በማፍላት እና በመትከል እንዲሁም ለማኀበረሰቡ ችግኞችን በማሰራጨት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
በላንቴ ቀበሌ በሚገኝ ተራራማ ስፍራ የተተከሉት ችግኞች ከስፍራው ተነስቶ ወደ አባያ ኃይቅ የሚገባውን ደለል ማስቀረት የሚያስችሉ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የጥበቃ ሥራዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች በተሻለ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውን አውስተዋል።
የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑት አቶ አብዮት ወቻ እና ወ/ሮ ፍጹም መኮንን ለተሻለ አካባቢ ጥበቃ ችግኞችን በመትከል ባበረከቱት አስተዋጽኦ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የኮሌጅ ዲኖች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ቡድን መሪዎች እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት አካላት ተሳትፈዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት