የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ‹‹Institute of Primary Health Care›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ከአራት ጤና ጣቢያዎች ለተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሥልጠና ከነሐሴ 12-16/2017 ዓ/ም ለ5 ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
‹‹Integrated Adolescent SRH Services, Peer Education and VCAT›› በሚል ርእስ በተሰጠው ሥልጠና ከሼቻ፣ ወዜ፣ ቆላ ሼሌና ዚጊቲ ባቆሌ ጤና ጣቢያዎች የተወጣጡ የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎችና በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕብረተሰብ ጤና መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ንጉሤ ቦቲ እንደገለጹት ሥልጠናው ከዚህ ቀደም በወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተከናወነ የምርምር ውጤትን መነሻ በማድረግ እንዲሁም ከወጣቶችና ከጤና ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ውይይት በዘርፉ ላይ የተለዩ ችግሮችን ለመድፈን የተዘጋጀ ነው፡፡ ዶ/ር ንጉሤ የወጣቶች የእድገት ለውጦችና ደረጃዎች፣ የተቀናጀ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶች እና የአቻ ለአቻ ትምህርት አሰጣጥ ዘዴዎች በሥልጠናው የተዳሰሱ ርእሰ ጉዳዮች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
በጤና ተቋማቱ የሚሰጠውን የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት የተሻለና ለወጣቶች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል የሥልጠናው ዋና ዓላማ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ንጉሤ ለወጣቶች የተሳለጠና ምቹ አገልግሎት በተቋማቱ እንዲኖር ማድረግ ከሥልጠናውና በቀጣይ በፕሮጀክቱ በሚሠሩ ሥራዎች የሚጠበቅ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ምቹና ማራኪ ማድረግ እንዲሁም የአቻ ለአቻ ትምህርትን ማጠናከር በትኩረት የሚሠራባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ ወጣቶች የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤናን የተመለከቱ መረጃዎችን የሚያገኙበትና ቀጠሮ የሚይዙበት ነጻ የስልክ መስመር አገልግሎት በጤና ጣቢያዎቹ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም ወቅቱ የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጉዳይ ትኩረት የተነፈገውና መዘናጋት የሚታይበት እንደመሆኑ ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በመቅርጽ የተጀመረውን ሥራ በሌሎች የጤና ተቋማት ለማስፋት እንደሚሠራም ዶ/ር ንጉሤ አረጋግጠዋል፡፡
የሼቻ ጤና ጣቢያ ኃላፊ ሲ/ር አሰለፈች ጉደታ በሥልጠናው የወጣቶች ሥነ ተዋልዶ አገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርዶች ላይ በቂ ግንዛቤ ያገኙበትና አገልግሎቱን ለወጣቶች በተቀናጀ መንገድ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ጠቃሚ ዕውቀት የገበዩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሥልጠናው የተገኙ ግንዛቤዎችን በመጠቀም ለወጣቶች ከአቀባበል ጀምሮ ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ተቋማቸው እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
የዚጊቲ ባቆሌ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ እድሉ ሳሙኤል በጤና ጣቢያቸው የወጣቶች ሥነ ተዋልዶ መስጫ ክሊኒክ መኖሩን ገለጸው ሥልጠናው በቀጣይ የክሊኒኩን የሥራ እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ከሥልጠናው ተገንዝበናል ያሉት ኃላፊው በጤና ጣቢው የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል ባሻገር ወጣቶች ወደሚገኙበት ት/ቤቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት ወዘተ ድረስ በመሄድ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሁም ወጣቶች በጤና ጣቢያው ያለውን አገልግሎት እንዲጠቀሙ እንሠራለን ብለዋል፡፡
የቆላ ሼሌ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ባሕሩ በደዳ በበኩላቸው ሥልጠናው ከዚህ ቀደም በወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ላይ በጤና ጣቢያችን የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያሻሽልና ከወቅቱ ጋር አብሮ እንዲሄድ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ከሥልጠናው የተገኘውን ግንዛቤ በመጠቀም የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር በተቀናጀ መንገድ እንዲሰጥ፣ የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎችን ለወጣቶች ምቹና ማራኪ የማድረግ ሥራ እንዲሁም በት/ቤቶች የሥነ ተዋልዶ ክበባት እንዲጠናከሩ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት