የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ማስማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኞች "አንድነት ለተሻለ ተቋም ግንባታ" በሚል መሪ ቃል የአብሮነት መርሃ ግብር ሐምሌ 6/ 2017 ዓ/ም የተካሄደ ሲሆን የ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑንም ኮሌጁ ገልጿል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ኮሌጁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በተማሪዎች ተመራጭ የትምህርት ተቋም ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ገልጿል። በዕለቱ በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች እና ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማትም ተሰጥቷል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በተቋም ሠራተኞች መካከል የሚኖር መግባባት፣ ትብብርና አንድነት ለተቋማት ዘላቂ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ከተመሠረተ ሃያ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ዓመታት የቀሩት የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ልምድ የሚቀስሙበት ማዕከል እየሆነ መጥቷል ያሉት ዶ/ር ተክሉ ኮሌጁ በ 2017 በጀት ዓመት በሁለት ፕሮግራሞች ሀገር አቀፍ አክሪዲቴሽን ማግኘቱ እንዲሁም በሁለት ዘሮች በተሰጠው ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና 100% እና 98% ተማሪዎችን ማሳለፍ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል:: በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፉም ኮሌጁ ስኬታማ ትግባራትን ያከናሆነ ሲሆን ለአብነት በዚህ ዓመት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች በታወቁ የምርምር መጽሔቶች ላይ ካሳተሟቸው 630 የምርምር ሥራዎች መካከል 107 የሚሆኑት የዚሁ ኮሌጅ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ያሉ ስኬቶችን ማስቀጠልና ሌሎች ተጨማሪ ፕሮግራሞች ዕውቅና እንዲያገኙ መሥራት ይገባል ያሉት ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው የማስማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉን በቅርቡ ተኝቶ ሕክምና በከፊል እንዲጀምር ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል። ዶ/ር ተክሉ ኮሌጁ ላስመዘገባቸው ስኬቶች ሁሉ የተቋሙ ሠራተኞች ለተወጡት ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቪ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ የዕለቱ መርሐ ግብር እንደ ኮሌጅ የተጀመሩ ሥራዎችን ፣ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝብ የተሰጡ ተግባራትን ለማሳካትና አጠናክሮ ለመቀጠል የሠራተኞችን የእርስ በእርስ ትብብርና ተግባቦት ለማጠናከር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። ኮሌጁ በሶስት የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ሥራ የጀመረ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ደስታ አሁን ላይ በ10 የመጀመሪያ፣ በ17 የ2ኛ እንዲሁም በአንድ የሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ከ2000 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው ብለዋል። የ2017 በጀት ዓመት እንደ ኮሌጅ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ያሉት ዶ/ር ደስታ በፕሮግራም ዕውቅናና በተማሪዎች የመውጫ ፈተና የተመዘገቡ ስኬቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል። የኮሌጁ የምርምር ዘርፍ በማኅበረሰባችን ችግሮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ ምርምሮች እየተካሔዱ ሲሆን በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፉም ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል::
በኮሌጁ የሚገኘው ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዘርፈ ብዙ ከምርምር ያለፉ ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት ዶ/ር ደስታ ማዕከሉ በቅርቡ የተከበረውን የዓለም የቆዳ ጤና ቀንን በማስመልከት በቆጎታ ወረዳና በአርባ ምንጭ ከተማ ቦላ ጉርባ ቀበሌ ለ25 ሺህ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ፣ ለ500 ሰዎች ምርምራ፣ እንዲሁም ለ337 ሰዎች የተሟላ የቆዳ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱ የሰዎችን ሕይወት የዳሰሰ ተግባር መሆኑን አንስተዋል። ኮሌጁ ፈረንሳይ ሀገር ከሚገኘው ከኦፕቲካል ሴንተር ወርልድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ እና አካባቢው ለሚገኙ 7, 200 ለሚሆኑ የማኀበረሰብ ክፍሎች የተሰጠውን ነፃ የዐይንና ጆሮ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በንግግራቸው ያነሱት ዶ/ር ደስታ በዚሁ አገልግሎት ከ150 ሚሊየን ብር በላይ ለዘመቻው መሳካት ጥቅም ላይ መዋሉን ተናግረዋል። ዶ/ር ደስታ ለተመዘገቡ ስኬቶች የኮሌጁ እና የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለተወጡት ሚናና ላሳዩት ትጋት በኮሌጁ ማኔጅመንት ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው "በተገኙ ስኬቶች ሳንኩራራ እና ሳንዘናጋ ሁላችንም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ራሳችንን ለተሻለ ፈተና እናዘጋጅ" ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዕለቱ በኮሌጁ በ 2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎች እና ግለሰቦች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
ከመርሐ ግብሩ ጎን ለጎን የደም ልገሳ የተካሔደ ሲሆን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጁ የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራንን፣ ተመራማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የጋሞ አባቶች፣ የሐይማኖት መሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በፕሮግራሙ ተገኝተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት