አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹Horizon Europe Africa Initiative›› እና ‹‹Euraxess›› ጋር በመጣመር የአውሮፓ ኅብረት የምርምር ድጋፍ ዕድሎችንና ትስስሮችን አስመልክቶ ለተመራማሪዎች ተግባራዊ ግንዛቤ በማስጨበጥ የምርምር አቅምን ለማጎልበትና የፈንድ ዕድሎችን ለማሰስ ያለመ የ‹Horizon Europe› የመረጃ ቀን እና ግራንት አጻጻፍ ወርክሾፕ ጥር 19/2018 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የመማር ማስተማር፣ ምርምርና፣ የማኅበረሰብ ጉድኝት ተልእኮዎችን ይዞ ከቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፋዊነት የራእዩ ማእከላዊ ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ዕውቅናና ሽልማቶችን ያስገኙለት በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮች ያሉት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ ይህ የምርምር ድጋፍና የትስስር ዕድል የምርምር ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራትና ስፋት እንዲያከናውን በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም መምህራንና ተመራማሪዎች ከመርሐ ግብሩ የሚያገኙትን ተግባራዊ ጥቆማዎች ተጠቅመው ብቁ ፕሮፖዛሎችን በማዘጋጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የላቁ የምርምር ፕሮጀክቶችና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ከማሳደግ አንጻር በልዩ ትኩረት በሚሠራበት በዚህ ጊዜ ወርክሾፑ መካሄዱ ወቅቱን የዋጀ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲያችን ከ80 በላይ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የትብብር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ለዚህም በበርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ሽልማቶችና ዕውቅናን ያገኙ ተመራማሪዎችን ይዘን ይህንን ዕድል በመጠቀም ይበልጥ ስኬታማ ለመሆን እንሠራለን ብለዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች በዓለም አቀፍ የምርምር ድጋፍ ፕሮግራሞች ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው ይህ ወርክሾፕም ከማሳያዎቹ አንዱና ጠንካራ ሃሳቦችን ወደ ተወዳዳሪ ፕሮፖዛሎች ለማሳደግ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አማካሪ ሚኒስትር Dr. Laurent Bocheru የአውሮፓ ኅብረት ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በትምህርትና በምርምር የሚያደርገውን ድጋፍና የትብብር ሥራዎች በተለይም በ‹‹Horizon Europe Africa Initiative IV›› ያሉ የምርምር ዘርፎችና የወጡ ጥሪዎች ላይ ስኬታማ ፕሮዛሎችን ማቅረብን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ኅብረቱ ለምርምር ድጋፍ ትልቅ በጀት የሚመድብ ቢሆንም በተሳትፎ ደረጃ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራትና ተቋማት ብቻ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ያነሡት ዶ/ር ሎውረን የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በቂ መረጃ ይዘው የተሻለና ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰርና የ‹‹Euraxess Africa›› የአፍሪካ ተወካይ ዶ/ር የድልፋና ሰጥአርጌ እንደገለጹት ‹‹Horizon Europe›› በዓለም ትልቁ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ሲሆን የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትና ተመራማሪዎች ጋር በጋራ በመሆን በፕሮግራሙ እንዲሳተፉና የድጋፍ እድሎችን እንዲያገኙ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ወርክሾፑ ተዘጋጅቷል፡፡
ዓላማችን በበርካታ ዘርፎች ብቁ ተወዳዳሪዎች ቀርበው የምርምር ድጋፉን ወደ አፍሪካ ብሎም ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመጡና ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው ያሉት ዶ/ር የድልፋና በመርሐ ግብሩ ተመራማሪዎች የምርምር ጥሪዎችን የሚያገኙበት፣ ከተለያዩ በዓለማችን ያሉ ተመራማሪዎች ጋር የሚገናኙበትና ተቀባይነትን የሚያገኙ ፕሮፖዛሎችን የሚያጋጁበትን መንገድ ላይ በተግባር የተደገፈ ማብራሪያ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ተመሳሳይ መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሀገራዊ ምርምር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሀብታሙ አበራ ባስተላለፉት የበይነ መረብ መልእክት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሳይንስና ፈጠራዎችን ለማሳደግ እና ምርምሮችን ለማስፋፋት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ከምታደርገው መስተጋብር አንዱ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላት ትስስር መሆኑን ተናግረው የ‹‹Horizon Europe›› ፕሮግራም የድጋፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የትስስር ማእቀፍ ነው ብለዋል፡፡ ወርክሾፑም ግንዛቤ የሚያስጨብጥና ዘላቂ የትብብር ትስስር ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ግራንትና ኮላቦሬቲቭ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ኃይሉ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በኢኒሼቲቩ ሁለት ፕሮጀክቶችን አማሸነፉን ጠቁመው በምርምር ያለውን አቅምና በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸውን ስኬታማ ምርምሮች ከግምት በማስገባት መረጃ በመስጠትና በማብቃት የአመልካቾችን ቁጥርና ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ብሎም ትስስር በመፍጠር በጋራ ለመሥራት ወርክሾፑ መዘገጀቱን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ሲሆን በቂ ግራንትና የትብብር ፕሮጀክቶች ማምጣት ግድ ይለዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ‹‹Horizon Europe Africa Initiative›› በዚህ ዓመት ባወጣው 4ኛው የምርምር ድጋፍ ጥሪ መሠረት ጥሩ መጻፍ የሚችሉ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች ከጀማሪ ተመራማሪዎች ጋር በመጣመር ብቁ ፕሮፖዛል አዘጋጅተው እንዲወዳደሩ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶ/ር አሸናፊ በወርክሾፑ ተመራማሪዎች የግራንት አጻጻፍና የአፕሊኬሽን አሞላል ቴክኒኮች ላይ ከተደረገላቸው ገለጻ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በማመልከቻ ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችን በመለየት ጥራት ያለው ፕሮፖዛል ማቅረብ የሚቻልበት መንገድ የተዳሰሰ ሲሆን ቀደም ሲል የነበረውን የአመልካቾች ቁጥር በማሳደግ የማሸነፍ ዕድልን ከፍ ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት




