የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ‹‹በጎ ፈቃደኝነት ለጤናማ ማኅበረሰብ›› በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 12/2017 ዓ/ም ጀምሮ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ ማኅበረሰብ ነጻ የክረምት በጎ ፈቃድ የጤና ምርመራ፣ የምክር እና ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምሑራንን እና ባለሙያዎቹን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ዘርፈ ብዙ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መርሐ ግብሩን ላዘጋጁት የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አመራር አካላትና ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ዓመታት ለማኅበረሰቡ ዕውቀትን በማስታጠቅ፣ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር በመለየትና መፍትሔ በመፈለግ እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር በማዋሐድ ሰፊ ተግባር ማከናወኑን ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል መጠለያ ለሌላቸው አረጋውያን የመጠለያ ቤቶችን በማደስና በመሥራት፣ የአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ እንዲሁም የደም ልገሳ መርሐ ግብር በማዘጋጀት የተከናወኑት ተግባራት ተጠቃሾች መሆናቸውን አክለዋል። ‹‹ጤና ካለ ሁሉም አለ›› ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዘንድሮው ክረምት ያዘጋጀው ነጻ የሕክምና አገልግሎት መርሐ ግብር የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እንደገለጹት መርሐ ግብሩ በጤና ሚኒስቴር አነሳሽነት በጤናው ዘርፍ በክረምት የሚከናወን የበጎ አድራጎት ተግባር ነው። ለማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ነጻ የምርመራና ሕክምና አገልግሎት መስጠት ቀዳሚው መሆኑንና ለዚህም በቂ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በነጻ የምርመራና ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡትን የምክር አገልግሎቶች መተግበር እንደሚገባውም አጽንዖት ሰጥተዋል።
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና አገልግሎት ም/ኮርፖሬት ዳይሬክተር እንዲሁም የአገልግሎቱ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙሉቀን ብርሃኑ እንደገለጹት ከነሐሴ 12/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በቆየው ነጻ የምርመራና ሕክምና አገልግሎት እና የደም ልገሳ መርሐ ግብር የዐይንና የኩላሊት ምርመራና ሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ የሥነ አእምሮና ማማከር፣ የአጥንትና መገጣጠሚያ እንዲሁም የአልትራሳውንድ እና ሌሎች የላቦራቶሪ ሕክምና አገልግሎቶች ተደራሽ መደረጋቸውንና በዚህም ከ1ሺህ 100 በላይ የሚሆኑ የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከበጎ ፈቃደኞች 28 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም አክለዋል።
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ የዘንድሮው ነጻ የምርመራና ሕክምና አገልግሎት መርሐ ግብር በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በመርሐ ግብሩ ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው ደም በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ለሕክምና አገልግሎት የሚውል መሆኑንም ገልጸዋል።
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ረ/ፕ ገሊላ ቢረሳው የማኅበረሰቡን ጤና ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው እና አገልግሎቱ የማኅበረሰቡን የጤና ጫና መቀነስና የበሽታዎችን ተላላፊነት መግታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ ጉርባ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘርይሁን በትሬ እና የሼቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ልክነሽ አበራ ባገኙት አገልግሎት መደሰታቸውንና አገልግሎቱ አቅም ለሌላቸው ሰዎች በእጅጉ አጋዥ በመሆኑ ተግባሩ ሊቀጥል እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት