በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአይ ዩ ሲ ፕሮጀክት ንዑስ ፕሮጀክት 5 ከጋሞ ዞን ሰባት ወረዳዎች ለተወጣጡ 50 የሚሆኑ ሞዴል አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች እንሰትና ወተት እንዲሁም የእንስሳት መኖን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ያለመ "Innovative Strategies To Boost Enset Productivity And Strengthen Dairy Feed Security In Gamo Zone" በሚል ርእሰ የተዘጋጀ የአሠልጣኞች ሥልጠና ከጥር 20- 22/2018 ዓ/ም ድረስ በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በሥልጠናው የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ግብርና ለሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው የግብርና ሳይንስ መስክም የዩኒቨርሲቲው 2ኛው የትኩረት መስክ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንሰት ባሁኑ ወቅት የትኩረት መነሻም መዳረሻም እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ዶ/ር ተክሉ በዚህም እንደ ዩኒቨርሲቲ በሰራነው ጠንካራ ስራ እንስት በግብርና ሚኒስቴር ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የIUC ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በምርምር የተገኙ ዕውቀቶችን ወደ መሬት በማውረድና ለማኅበረሰቡ በማሸጋገር የሰዎችን ሕይወት መቀየር የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ፋሲል በየዓመቱ የሚሰጡ መሰል ሥልጠናዎችን የወሰዱ አርሶ አደሮች ያገኙትን ዕውቀት በምንያህል ደረጃ ወደ ተግባር መቀየራቸውና ውጤት ማስመዝገባቸው ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ግብርናን ጨምሮ በ7 ዘርፎች ላይ እንደሚሰራ የገለጹት ዶ/ር ፋሲል የተመረጡ አርሶ አደሮችን አምጥቶ በሳይንስ የተገኘውን ትክክለኛ መረጃ ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር አዳምሮ ወደ መሬት እንዲወርድ ማስቻል ዘላቂ ልማትን ለመስመዝገብ በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ ሰልጣኞች በሥልጠናው የወሰዷቸው ሃሳቦችና አዳዲስ አሰራሮች ለረዥም ጊዜያት በኮሌጁ የተመራማሪዎች ቡድን ምርምር ሲሰራባቸው የቆዩና ውጤታማነታቸው በተግባር የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ሰልጣኞች በተገኘው የምርምር ውጤት መሠረት ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ጭምር በማካፈል እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተርና የIUC ንዑስ ፕሮጀክት 5 ዋና መሪ እንዲሁም የሥልጠናው ሰጪ ፕሮፌሰር ይስሃቅ ከቸሮ ሥልጠናው የተዘጋጀው በዋናነት ምርምርን መሠረት ያደረጉ ምርጥ አሠራሮችን ለአርሶ አደሮችና ለባለሙያዎች ለማስተላለፍ መሆኑን ገልጸው ዓላማውም ዘላቂ የእንሰት ምርትን ማረጋገጥና የእንስሳት መኖ ደህንነትን ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘመናዊ በሆነ መልኩ የእንስሳት መኖን ማምረት፣ መኖ ማቀነባበር፣ የበለጸጉ ሀገራት የሚጠቀሙትን የማቀነባበር ዘዴን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ተሞክሮውን በምርምር በማስደገፍ ማውረድ፣ የተሻሻሉ የገፈራና የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ አዘገጃጀት በሥልጠናው የተሰጡ ርእሰ ጉዳዮች መካካል መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
የሆርቲካልቸር ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር ገዛኸኝ ጋሮ ሥልጣናቸውን ከእንሰት ምርትርታማነት ላይ ትኩረት በማድረግ የሰጡ መሆኑን ገልጸው ንጹህና ከበሽታ የጸዱ የእንሰት ችግኞችን በአርሶ አደር ደረጃ ማዘጋጀትና ማባዛት ዘዴዎች፣ መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ትንክክለኛ የፍግ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ላይ ትኩረት በማድረግ ሥልጠናውን የሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው አሠልጣኝ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ የምርምራቸው ትኩረት በሆነው የእንሰት አጠውልግ በሽታ/Bacterial Wilt/ ምልክቶች፣ መተላለፊያ መንገዶች እና የመከላከያና የመቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የእንሰት አጠውልግ በሽታ ምልክቶችን በቀላሉ መለየት፣ የበሽታውን ባሕርይ፣ የመተላለፊያ መንገዶችና የሚያባብሱ ነገሮች፣ የመከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ የአርሶ አደሩን ልምድና ሳይንሳዊ ግኝቶችን በማጣመር በሥልጠናው መዳሰሱን ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት ሥነ ምግብ ተመራማሪ የሆኑት አሠልጣኝ ዶ/ር አሸናፊ አዛገ የመኖ ማቆያ ዘዴ ላይ ትኩረት አድረገው ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በዋናነት የበቆሎ አገዳና ሌሎች ዕፅዋትን በአረንጓዴነታቸው አየር በማያስገባ መንገድ በማብላላት የሚገኘው ገፈራ/Silage/ አዘገጃጀት ላይ ተግባራዊ ሥልጠና የሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል:: በሀገራችን በሞቃታማ ጊዜ 35 ከመቶ የወተት ምርት እንደሚቀነስ የጠቆሙት ዶ/ር አሸናፊ የእንስሳት መኖን በገፈራ ማቆየት የመኖ እጥረት በሚፈጠር ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል በመሆኑ የምርት መቀነስን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የመጣችው ሰልጣኝ መሠረት ወልዴ በመሰል ሥልጠና ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ መሆኑን ጠቅሳ ወደ አካባቢዋ ሄዳ ያገኘችውን ዕውቀት ለሌሎች እንደምታጋራ ገልጻለች፡፡ ሥልጠናው በተለይ የእንሰት አያያዝና ንጹህ የሆኑ የእንሰት ችግኞችን እንዴት ማባዛትና የእንሰት አጠውልግ በሽታን በምን መልኩ መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤን እንደሰጣት ተናግራለች፡፡
ከቦረዳ ወረዳ የመጣው ሌላኛው ሰልጣኝ ጴጥሮስ ቱንጄ የእንሰት አጠውልግ በሽታ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ የከብቶች እርባታና መኖ ማዘጋጀት ላይ ከሥልጠናው ተግባራዊ ግንዛቤ ያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት




