አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የጥናትና ምርምር ጆርናሎች "OMO International Journal of Sciences" እና "Ethiopian International Journal of Engineering and Technology" በትምህርት ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ ዕውቅና (Accreditation) ማግኘታቸውን እንዲሁም ቀደም ሲል ዕውቅና የነበረው "Ethiopian Journal of Water Science and Technology" ለሁለተኛ ጊዜ ዕውቅናው እንዲታደስ መደረጉን ተከትሎ ዛሬ መጋቢት 10/2018 ዓ/ም ለጆርናሎቹ ኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት የዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የሦስተኛ  ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተያዘላቸው ጊዜ እንዳያጠናቅቁ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ጥናቶቸቸውን የሚያሳትሙበት ዕውቅና ያለው ጆርናል ጉዳይ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የዩኒቨርሲቲው ጆርናሎች ዕውቅና ማግኘት ተማሪዎችና መምህራኖቻችን ጥናቶቻቸውን በወቅቱ እንዲያሳትሙ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል። 

ዕውቅናው  በትምህርት ሚኒስቴር የተቀመጡ ሌሎች ቁልፍ ተግባራትን በአግባቡ እንድናከናውን መነሻና አነሳሽ ይሆነናል ያሉት ፕሬዝደንቱ የተቋሙን ተአማኒነት በማሳደግ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት አብረው እንዲሠሩ የሚያደርግ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል። ይህን ስኬት ለማስቀጠል ብሎም ከፍ ወዳለ ደረጃ  ለማሳደግና ዕውቅውን ዓለም አቀፍ ለማድረግ ከወዲሁ ሥራ መጀመር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ስኬቱ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የሁሉም ጆርናሎች ኤዲቶሪያል ቦርድ አባላትና ቺፍ ኦዲተሮች፣ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ የምርምር ኅትመት ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት፣ ለICT ዳግሬክቶሬት እንዲሁም ለሥራው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ፕሬዝደንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የምርምርና ትበብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት የትምህርት ፕሮግራሞች፣ የላቦራቶሪዎች እና የጆርናሎች አክሬዲቴሽን በቁልፍ ተግባራት አመላካች (KPI) ከተቀመጡ ሥራዎች ውስጥ ናቸው። ዕውቅና ማግኘት የትምህርትና ምርምር ተቋማትን ሥራ ጥራትና ተአማኒነት የሚያረጋግጥና የሚያሳድግ፣ የተመራቂ ተማሪዎችን ተቀባይነት የሚጨምር፣ ለትብብር ሥራዎችና የገንዘብ ድጋፎች በር የሚከፍት እና ተከታታይነት ያላቸው መሻሻሎችን የሚያመጣ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በሁለት የሕክምናና ጤና ሳይንስ የትምህርት ፕሮግራሞች አክሬዲቴሽን ማግኘቱን ያስታወሱት ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው በጆርናሎቹ ያገኘው ዕውቅና ለተቋሙ ቀጣይ ሥራዎች መነቃቃት የሚፈጥር እና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑን ተናግረል። ዕውቅና የማግኘት ሂደት ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍልና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሥራውን በትጋት በማካሄድ ለስኬት እንዲበቃ የበኩላቸውን ላበረከቱ ሁሉ ም/ፕሬዝደንቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የምርምር ኅትመት ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምዖን ዳርኬ የዩኒቨርሲቲው ጆርናሎች ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም እና ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመር ጆርናሎቹ እንዲሻሻሉና እንዲዳብሩ መደረጉን እንዲሁም የጆርናሎቹ ዌብሳይቶች በይዘትና በገጽታ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ መሠራቱን ገልጸዋል። 

በዕውቅና ሂደቱ የትምህርት ምኒስቴር ጥሪን ተከትሎ በሚኒስቴሩ መመዘኛ መሠረት የምዝገባ ማመልከቻው መግባቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው ካሉት አምስት ጆርናሎት አራቱ "B" ግሬድ ዕውቅና ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ለጆርናሉ ዕውቅና ማግኘት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት