በኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ የገንዘብ ድጋፍ እና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ከ12.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የተገነባው ዘመናዊ 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትላንት ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ከዚህ ቀደም በቀበሌው በደረሰው አሳዛኝ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት በሰው ሕይወት፣ በንብረትና በማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። ይህንን አስከፊ ጠባሳ ለማከምና በፕላስቲክ ሸራ ሥር ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ሲማሩ የነበሩ ሕፃናትን ወደ ምቹ የትምህርት ገበታ ለመመለስ ታስቦ የተገነባው ይህ ትምህርት ቤት፤ በሦስት ብሎኮች የተከፋፈሉ ዘጠኝ የመማሪያ ክፍሎችን የያዘ ነው።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ አደጋው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረ እንደመሆኑ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ መላው ሕዝብ በአንድ ልብና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መንቀሳቀሱን አስታውሰዋል። መድረኩም ለተፈጠረው አደጋ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት በትምህርት ዘርፍ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት በመሥራት ይህንን ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

ትምህርት ሕልምን የምንቀርፅበት መዳረሻ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሳሙኤል የትምህርት ቤቱን ግንባታ ኃላፊነት ወስዶ ለሰራው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። ተቋሙ መደበኛ ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን የምናስታውስበት ቋሚ የመጽናኛ ሐውልት ሆኖ ልጆቻችንን የምንቀርፅበት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል። ግንባታው በጥራት መጠናቀቁን አድንቀው፣ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በመድረኩ በኩል ትምህርት ቤቱን በአስፈላጊ ግብዓቶች ለማሟላትና ምድረ ግቢውን ለሕፃናት ምቹና ማራኪ ለማድረግ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል በበኩላቸው ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገትና ዘላቂ ብልፅግና ወሳኝ መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቀ ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረቀው ትምህርት ቤት ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ አካል መሆኑን ያነሱት ፕሬዝደንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው የራሱን የሲቪል መሐንዲሶችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ዕውቀትና ጉልበት በቀጥታ በመጠቀም እንዲሁም የግንባታ ግብዓቶችን በራስ ከገበያ በማቅረብ ሥራው ያለ ምንም ብክነት በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ማድረጉንና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል። ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ለዚህ ታላቅ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ፣ ለጎፋ ዞንና ለገዜ ጎፋ ወረዳ አመራሮች፣ ለሳውላ ካምፓስ፣ ለዩኒቨርሲቲው የምሕንድስና ትምህርት ክፍልና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እንዲሁም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምስጋና አቅርበዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ማኅበረሰብን ማገልገል ለራስ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ዩኒቨርሲቲው ቦታ፣ ክልልና ዞን ሳይገድበው በርካታ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱ ግንባታ ለአንድ ፕሮጀክት ስኬት ከሰብዓዊነት ባሻገር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን፣ በመተባበር ችግርን መቅረፍ እንደሚቻል እና በውስን በጀት ትልቅ ፕሮጀክት መሥራት እንደሚቻል ያሳየና የተማርንበት መሆኑን አስረድተዋል።አያይዘውም ለፕሮጀክቱ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ለሳውላ ካምፓስ፣ ለፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደፋሩ ደበበ እና ለተለያዩ የሥራ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ በበኩላቸው አደጋው በተከሰተ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከህዝቡ ጎን መቆሙ ትልቅ ብርታት እንደሆነ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው 6 ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ትምህርት ቤት መገንባት 270 ሕፃናትን በፕላስቲክ ሸራ ውስጥ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ከመማር ያወጣና ለተማሪዎች፣ ለወላጆችና ለመምህራን ታላቅ እፎይታ የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ትምህርት ቤቶችን በቁሳቁስ የመደገፍ ሥራ ትኩረት እንደሚሻ አሳስበዋል።

"ባገኘነው ዕድል ሁሉ ኅብረተሰባችንን እናገልግል" የሚል መርህ አንግበን እየሰራን ነው ያሉት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደምም የፀሐይ ኃይል (ሶላር) እና አነስተኛ የውኃ ኃይል ማመንጫዎችን በማቅረብ፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን የሕዝቡን ሕይወት የሚቀይሩ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውሰዋል። ተቋሙ በዘላቂነት እንዲያገለግልም ማኅበረሰቡ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ አቶ ደፋሩ ደበበ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ የሥራ ሂደት፣ የበጀት አጠቃቀምና በግንባታው ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ሪፖርት አቅርበዋል። ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ስኬት ከኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ከተገኘው 10 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 2.5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ አጠቃላይ ሥራው እንዲጠናቀቅ ማድረጉን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት ላልተቋረጠ ድጋፋቸው የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮችን አመስግነዋል።

በመርሐ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይም ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ስኬት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ለፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ደፋሩ ደበበ እና ለተለያዩ የሥራ ክፍሎች የዕውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ፣ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የዞኑና የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university             

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት