የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ከዚህ ቀደም የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰበት ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ዛሬ መጋቢት 6/2017 ዓ/ም አስቀመጠ ፡፡ ምክክር መድረኩ ለት/ቤቱ ማሰሪያ የሚሆን ከ23 ዩኒቨርሲቲዎች የተዋጣ 10 ሚሊዮን ብር አስረክቧል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ከጥቂት ወራት በፊት በማኅበራሰቡ ላይ የደረሰውን አስደንጋጭና ልብ ሰባሪ አደጋ ተከትሎ እንደ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ለማገዝ እና ለማቋቋም የተደረገውን ርብርብ አድንቀዋል። አደጋው በደረሰበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በወቀቱ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ዶ/ር ሳሙኤል አስታውሰዋል። አሁን ላይ በአካባቢው ህፃናት የሚማሩበት ሁኔታ ልብ የሚነካ ነው ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል ተማሪዎቹ ከዚህ በተሻለ መንገድ እንዲማሩ ለማድረግ ት/ቤቱን መገንባት አስፈልጓል ብለዋል። የግንባታ ሥራውን በአስቸኳይ በማጠናቀቅ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ት/ቤቱን ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ያሉት ሰብሳቢው ለዚህም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራውን በበላይነት ያስተባብራል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው አደጋው እንደተከሰተ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን መወጣቱን አስታውሰዋል። በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ አማካኝነት በተሰበሰበ ገንዘብ የመኖሪያ ቤት ለመሥራት ታስቦ እንደነበር የገለጹት ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ በአካባቢው መኖሪያ ቤት ዋነኛ ችግር አለመሆኑ በመረጋገጡና የአካባቢው ሕፃናት የሚማሩት ሁኔታ ምቹ አለመሆኑ ታውቆ ት/ቤት ለመገንባት መወሰኑን አብራርተዋል:: አ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የት/ቤቱን ግንባታ ሥራ እንዲያስተባብር እና እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብና አስተዳደር ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል::
የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊና የዞኑ አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ደመላሽ ብላቴ በአካባቢው በደረሰው አስከፊ አደጋ የትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች በእጀጉ መጎዳታቸውን ገልጸዋል። ችግሩን ለመቅረፍና ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በሸራ በተሠሩ ክፍሎች ውስጥ እንዲማሩ ተደርጓል ያሉት ተወካዩ ይህንን ችግር ተረድቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ት/ቤቱን በተሻለ ለመሥራት ላደረገው ድጋፍ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምሥክር ምትኩ በትምህርት ቤቱ 257 መደበኛና 61 ቅድመ መደበኛ ተማሪዎች የሚማሩበት ሲሆን በአደጋው ምክንያት ተማሪዎቹ ከሸራ በተሰሩ ክፍሎች እየተማሩ መሆኑን አውስተዋል። ትምህርት ቤቱ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲያች ትብብር የተሠራ መሆኑ ታሪካዊና የተቋማቱ ስም በትውልድ ሲታወስ እንዲኖር የሚያያርግ መሆኑን ያወሱት አስተዳዳሪው መድረኩ ት/ቤቱን ለመሥራት ማሰቡና መሠረት መጣሉ ከችግሩ አንጻር ሲታይ ትክክለኛ ውሳኔ ነውም ብለዋል።
የት/ቤቱ ግንባታ ሥራ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚመራና ቁጥጥር የሚካሄድ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንትና የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ምክክር መድረክ ስብሳቢ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፣ የምክክር መድረኩ ቦርድ ሴክሬተሪያት ዶ/ር ግርማ ወሰኔ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ፣ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የመድረኩ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር ችሮታው አየለ፣ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘለቀ ዶሳ እና ሌሎች የዞን እንዲሁም የወረዳ አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት