የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከኮሪያ መንግስት የልማት ኤጀንሲ (KOICA) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ ከኤስዲፖ (ASDEPO) እና ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሐምሌ 04 ቀን 2018 . የተሰጠው ይህ ስልጠና በጾታ ላይ የተመሰረቱ ጥቃቶችና ተያያዥ ህጎች፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የነጻ የህግ ድጋፍ፣ የፍትህ ተደራሽነት እና የሪፈራል ስርዓት ትስስር ላይ ያተኮረ ነው። በስልጠናው ላይ ከኮንሶ ዞን፣ ከካራት ከተማ እና ከኮንሶ ዙሪያ ወረዳዎች የተወጣጡ ዳኞች፣ ዓቃቤያን ህግ፣ የፍትህ እና የሴቶችና ህጻናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ባለሙያዎች (Social Workers) የሥነ ልቦና አማካሪዎች፣ የህግ አስከባሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት / ተክሉ ወጋየሁ የሥልጠና መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለጹት፤ ዓለም ላይ ያሉ ህጎችና ፖሊሲዎች ተቀያያሪ በመሆናቸው ባለሙያዎች በሥራ ላይ ስልጠና ራሳቸውን ማብቃትና ወቅቱ የሚፈልገውን ዕውቀት መላበስ ይገባቸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰብ ጉድኝት አንጻር በኮንሶ ዞን ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን የገለጹት ምክትል ፕሬዝደንቱ፣ የህግ ትምህርት ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የነጻ ህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ቁጥር 25 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል። እነዚህ ማዕከላት ለእናቶች፣ ለህጻናት እና አቅም ደካማ ለሆኑ ወገኖች ከጽሁፍ ዝግጅት እስከ ጥብቅና አገልግሎት ድረስ ነጻ እገዛ እንደሚያደርጉም አብራርተዋል።

የማህበረሰብ ጉድኝትና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር / ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ኮንሶ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት (Catchment) አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮንሶ ካራት አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ የዚህ ነጻ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑንና በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የሕግ ትምህርት ቤቱ ዲን አቶ አብረሃም ክንፈ የፕሮጀክቱን ዋና ዓላማ ሲያብራሩ፤ በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ህጎች (በፍትሐ ብሔርና በወንጀል) ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በተመለከተ የባለድርሻ አካላትን አቅም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል። ስልጠናው ባለሙያዎቹ እርስ በርስ በመናበብና የጋራ ትስስር በመፍጠር የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን በጋራ ለመከላከልና ተጎጂዎችን ሪፈር (Refer) ለማድረግ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

 የሕግ ትምህርት ቤቱ የማህበረሰብ ጉድኝትና የኢንዱስትሪ ትስስር አስተባባሪ አቶ ጌትነት ደባልቄ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በተለይ ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ለተፈናቃዮች የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በካራት ዙሪያ፣ በዳሰነች፣ በሰገን ዙሪያ እና በአርባ ምንጭ ከተማ 4 አዳዲስ ማዕከላት ተከፍተው ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። በነዚህ ማዕከላት 8 ስልጠናዎችን ለመስጠት መታቀዱንና የመጀመሪያው በአርባ ምንጭ፣ ሁለተኛው ደግሞ አሁን በካራት ከተማ መሰጠቱን ገልጸው በቀጣይም የሁለተኛ ዙር ስልጠና እንደሚኖር አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህራን ማህሌት ደመቀ፣ ጆርጅ አላሶ እና ዳኛቸው ወርቁ የተሰጠው ይህ ስልጠና፤ የሴቶችና የህጻናት መብቶች፣ የሰብዓዊ መብት መርሆች፣ የህጻናት ተስማሚ የፍትህ መርሆች፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል እንዲሁም ወሲባዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ላይ ያተኮረ ሰፊ ዳሰሳ ያካተተ ነበር።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ስለ ህጻናትና ሴቶች መብት ጥበቃ እንዲሁም ጥቃቶች ሲያጋጥሙ ከተቋማት ጋር በቅንጅት እንዴት መስራት እንደሚቻል ሰፊ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከመሬት ይዞታና ከውርስ ህግ አንጻር ሴቶች ያላቸውን የመሬት ባለቤትነትና የማስተዳደር መብት በተመለከተ ጠቃሚ እውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የጥበብ ምንጭ!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት