በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ አስፈጻሚ /ቤት አስተባባሪነት በተቋቋመ ቡድን ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት ሚኒስቴርና በሥሩ ከሚገኙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ጋር የተፈራረመውን የቁልፍ ተግባራት (KPI) አፈጻጸም ያለበትን ደረጃ ለማወቅ የሚያስችል የውስጥ ሱፐርቪዥን  ከመጋቢት 29/2017 . ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የቆየ የውስጥ ምልከታ ተካሄደ፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

ምልከታው በሁሉም ካምፓሶች ቁልፍ ተግባራቱ የደረሱበትን ደረጃና ቀሪ ሥራዎችን በማወቅ በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጅክ ዕቅድ ሥራ አስፈጻሚና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ተናግረዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክተርና የምልከታው ቡደን አባል ዶ/ር ሠረቀብረሃን ታከለ በምልከታው ካምፓሶች ያላቸው አፈጻጸም ከዕቅዳቸው አንጻር ሲታይ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው የተፈጸሙ ተግባራትም በአግባቡ ተሰንደው መያዛቸውን መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ ለኢንስቲትዩቱ በተሰጡ ቁልፍ ተግባራት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው  ከውስጥ ግምገማ፣ ከፕሮግራም ዕውቅናና ከሥርዓተ-ትምህርት ክለሳ አንጻር በርካታ ሥራዎች የተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንሲቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በ2017 ዓ.ም የተሰጡ ቁልፍ ተግባራትን መነሻ በማድረግ  በምርምር፣ በመማር ማስተማር፣ በማኅበረሰብ ጉድኝትና በቤተሙከራ አክሪዲቴሽን ዙሪያ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዲጂታል ሊትረሲ ጉዳይ ከተሰጡን ዋና ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን ካሉን መምህራን መካከል 80 ከመቶ ያህሉ ሥልጠናውን መውሰዳቸውንና ቀሪ 20 ከመቶ መምህራንን በቀሪ ጊዜ ውስጥ ለማሰልጠን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ዶ/ር ሙሉነህ አክለዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እንደ ኮሌጅ ከሥራዓተ- ትምህርት ክለሳ፣ ከተማሪዎች ቅበላ እና ከትምህርት ፕሮግራሞች ዕውቅና አንጻር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው ለኮሌጁ የተሰጡ ቁልፍ ተግባራት በርካቶቹ በጥሩ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው እስከ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም ድረስ አፈጻጸሙን 90 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት