አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ጋር በመተባበር ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ የቤተ-ሙከራ ባለሙያዎችና መምህራን በቤተ-ሙከራ አደረጃጀትና ለአክሪዲቴሽን በሚያስፈልጉ መስፈርቶች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከመጋቢት 15-19/2017 ዓ/ም ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲሰጥ የነበው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
‹‹Laboratory Accreditation (ISO) International organization for Standardization or (IEC)››፣ ‹‹International Electro technique Commission 17025; 2017)››፣ ‹‹General Requirements for the Competency of testing and Calibration Laboratories(ISO/IEC) 17025; 2017›› ሥልጠናው ከተሰጠባቸው ርዕሶች መካከል ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት ዘመኑ የውድድር እንደመሆኑ አንደ ዩኒቨርሲቲ ያቀድንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምርምሮችን በትኩረት መሥራት፣ ቤተ-ሙከራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግና የመማር ማስተማሩ ሥራ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ በተቋማችን የሚሰሩ ሥራዎች ሁሉ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን ይገባቸዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ ያሉን ሥርዓተ - ትምህርቶችና ቤተ-ሙከራዎች ዕውቅና እንድያገኙ ማድረግ ራስ-ገዝ የምርምር ተቋም ለመሆን ለሚደረገው ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በ2017 ዓ.ም ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተሰጡን ቁልፍ ተግባራት (KPI) መካከል ያሉን ቤተ-ሙከራዎችን ዕውቅና ማስጠት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ አንጻር በዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ላይ ለሚሰሩ ሙያተኞች የተሰጠው ሥልጠና ለሥራው ስኬት አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ትምህርትን በተግባር የተደገፈ ለማድረግ የቤተ-ሙከራዎችን ደረጃና ጥራት ማሻሻል ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ተናግረዋል፡፡
የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ጌታሁን በተቋሙ የሚገኙ ቤተ-ሙከራዎች ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ በዘርፉ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ለቤተ-ሙከራ አክሪዲቴሽን በሚያስፈልጉ አደረጃጀቶችና ስታንዳርዶች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ሥልጠናው የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በየኮሌጁ ያሉ ቤተ-ሙከራዎችን በጋራ መጠቀም እንዲቻልና በአስፈላጊ ግብአቶች እንዲሟሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ዶ/ር ኤፍሬም ጠቁመዋል።
የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቁጥር ደረጃ በርካታ ቤተ-ሙከራዎች የሚገኙ ሲሆን ያሉ ቤተ-ሙከራዎች በየደረጃው ዕውቅና እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በሥልጠናው ሠልጣኞች ለዚህ ሥራ አጋዥ ግንዛቤ አግኝተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምርምሮች የሚሰሩባቸው ዕውቅና ያላቸው የተሟሉ ቤተ-ሙከራዎችን ለማደራጀት ይረዳል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት የላቦራቶሪ አክሪዲቴሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚና አሠልጣኝ አቶ ጌቴ ብርሃኑ ሥልጠናው ( ISO/IEC) 17025;2017) ላይ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን የቤተ-ሙከራ ዝግጅት መስፈርቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአክሪዲቴሽን የሚያስፈልጉ የአደረጃጀት ስታንዳርዶችን ለማስገንዘብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሥልጠናው በቤተ-ሙከራ አደረጃጀትና ለአክሪዲቴሽን በሚያስፈልጉ መስፈርቶች ዙሪያ አስፈላጊ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ቤተ ሙከራዎችን ዕውቅና ለማሰጠት ለሚሰራው ሥራ ጠቃሚ መሆኑን አውስተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት