አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹Action for Social Development and Environmental Protection Organization/ASDEPO/ ጋር በመተባበር ‹‹Building Adaptive Resilience for People Affected by Conflict and Climate Crisis focusing on Youth›› በሚል ርእስ በግጭትና የአየር ጠባይ ቀውስ የተጎዱ ሰዎች በተለይም የወጣቶች የመቋቋም አቅምን መገንባት ላይ ያተኮረ የትብብር ፕሮጀክት መጋቢት 17/2018 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በትብብር ለመሥራት ያስችለው ዘንድም ከ‹‹ASDEPO›› እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት እና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ብቸኛው የምርምር ዩኒቨርሲቲና የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረምን የሚመራ መሆኑን ጠቅሰው የተሰጠውን ተልእኮ ለማሳካት ወሳኝ ትብብሮችን መሥርቶ በጋራ ማቀድ፣ ሀብት ማፈላለግና መተግበር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ትብብሮችን እያስፋፋ የመጣ ሲሆን አሁን ላይ ከ102 በላይ መድረሳቸውን ዶ/ር ተክሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ተክሉ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው የወሳኝ ሀብቶች በተለይም የውኃ እና የሚታረስ መሬት እጥረት ምክንያት ግጭቶች፣ የምርት መስተጓጎል፣ የኢኮኖሚ ውጥረት፣ የሕይወት አደጋ ላይ መውደቅ፣ መፈናቀልና ስደት ሊከሰቱ የሚችሉ በመሆኑ ግጭት እና የአየር ንብረት ቀውሶች ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩና እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭት ምክንያት የሚመጡ ተግዳሮቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት ርእሰ ጉዳዮቹን ተደራሽ ያደረጉ ወቅታዊና የትብብር ሥራዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ይህ ፕሮጀክትም የዩኒቨርሲቲውንና የግብረ ሠናይ ድርጅቶቹን አቅምንና ዕውቀት በማጣመር ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥበት መሆኑን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በአቅራቢያው የሚገኙና ሌሎችም ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት ከበርካታ አጋሮች ጋር ትስስር እንደሚፈጥር ተናግረው በዚህ ረገድ ውጤታማ የትብብር ፕሮጀክቶችን በመተግበር የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር አብርሃም ክንፈ ፍትሕን ተደራሽ የማድረግ ሥራ የብዙዎችን ቅንጅትና የጋራ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረው ት/ቤቱ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለእስከ አሁኑ ስኬትና ለዘርፈ ብዙ ድጋፎች ለአጋር ተቋማቱ ምስጋና ያቀረቡት ዲኑ ለቀጣይ ትብበሮች ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ት/ቤቱ ሁሌም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ጤናው ጨርቆስ እንደገለጹት የፍትሕ ዘርፉን ለማሻሻል በተቋማቸው ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ የለውጥ ሥራዎች ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ2018-2022 ዓ/ም የሚተገበር አዲስ የፍትሕ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፍትሕ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ፣ በአስተሳሰብና በባለሙያ አቅም ራሱን ማሳደግና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት ያለበት በመሆኑ ለፍትሕ ሥርዓቱ አዲስ እይታ ለመፍጠርና ተቋማቱን በማሻሻል ለኅብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ምርምሮችን እያደረጉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ስምምነቱ ትልቅ መሠረት እንደሚጥል የተናገሩት ም/ኃላፊው ከአንጋፋው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ሆነ በርካታ ስኬቶች እያስመዘገበ ከሚገኘው የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት ጋር አብሮ ለመሥራት በመቻላችን እጅግ ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡
በASDEPO ተጠባባቂ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተርና የ‹‹Protection, Gender and Peace Building›› ቴማቲክ ዳይሬክተር ማኅሌት ዳምጠው ፕሮጀክቱ በዋነኛነት ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ አትኩሮ በዩኒቨርሲቲው በኩል ለተጠቂዎቹ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት በጋራ የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ተጨማሪ ሁለት ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቱን አስመልክቶ በ‹‹ASDEPO›› ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አብያለው ደሳለኝ እና በዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝትና ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር አስተባባሪ መ/ር ጌትነት ደባልቄ በቀረቡት ገለጻዎች እንደተመለከተው ግጭቶችና የአየር ንብረት ለውጥ ሲፈጠሩ የመጀመሪያ ተጠቂዎች ወጣቶች እንደመሆናቸው ፕሮጀክቱ ተጋላጮቹ ላይ ትኩረት በማድረግ በዋናነት በኮርያ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት(KOICA) በኩል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዳሰነች፣ ካራት ዙሪያና ሰገን ዙሪያ ወረዳዎች እና አርባ ምንጭ ከተማ ላይ የሚተገበር ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ሰለባ ለሆኑ የማኅበረሰብ አካላት፣ ለወጣቶችና ለተፈናቃዮች በተቀናጀ መልኩ ነጻ የሕግ ድጋፍ በመስጠት፣ በሀገራዊ የሰላም መግባባቶች በማሳተፍና አካታች የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎች በማዘጋጀት በራሳቸው አቅም ተቋቁመው ማኅበራዊ ደኅንነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስና ሥነ ተዋልዶን አስመልክቶ ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ መፍጠር፣ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት በራስ አቅም የመቋቋም እንዲሁም ሲከሰቱ የሥርዓ ጾታና ሥነ ተዋልዶ ጤናን አካተው እንዲሠሩ በየወረዳዎቹ የሚመለከታቸውን አካላት አቅም ማሳገድ፣ በየወረዳዎቹ የፈቃደኛ ወጣቶች ኮሚቴ በማቋቋም በተለያዩ ሀገራዊ ምክክሮችና የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ጥቃት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ነጻ የሕግና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች የሚሠሩ ይሆናል፡፡
ፕሮጀክቱ እንደ አጠቃላይ የሦስት ዓመታት ቆይታ የሚኖረው ሲሆን ለአንድ ዓመት ተግራዊ የሚደረግበት 10.5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ከአጋር ተቋማቱ ተገኝቷል፡፡ በወረዳዎቹ አዲስ የሚቋቋሙት አራት የነጻ ሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት የዩኒቨርሲቲውን የነጻ ሕግ ድጋፍ ማእከላት ቁጥር ወደ 24 ከፍ በማድረግ ተደራሽነቱን እንዲሚያሰፉም ተመላክቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ተሳታፊዎች በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ፍ/ቤት ሼቻ ምድብ ችሎት በሚገኘው የዩኒቨርሲቲው የነጻ ሕግ ድጋፍ ማእከል ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





