የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ተማሪዎች ማኅበር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሙቲንግ ማኅበር እና ከሕግ ት/ቤት ምስለ ችሎት ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹የኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነት መብት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ወይስ የግል? የተሻለው አማራጭ የቱ ነው?›› በሚል ርእስ ከኅዳር 11-12/2017 ዓ/ም ክርክር አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና የምስለ ችሎት/Moot Court/ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሀገረወርቅ ደሳለኝ መድረኩ ተማሪዎች የክርክር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና በመካከላቸው የሚኖረው መግባባት እንዲዳብር የሚረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕግ ት/ክፍል ኃላፊ መ/ር አብርሃም ክንፈ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የሚማሩትን ትምህርት በተግባር በመለማመድ ወደ ሥራ ዓለም ሲሰማሩ በሚያጋጥሟቸው ሙግቶችና ክርክሮች ሳይቸገሩ ፍርድ የመስጠት ክሂሎት እንዲያዳብሩ የክርክር መድረኩ የሚያግዛቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ መ/ር አብርሃም የአምሳለ ችሎት ውድድሮች በሀገር አቀፍ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ሲሆን መሰል የክርክር መድረኮችን ማዘጋጀት ተማሪዎች ለውድድሮቹ ብቁ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ መ/ር አብርሃም ቀደም ሲል በነበሩ ውድድሮች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አመርቂ ውጤት በማምጣት ተቋሙን ማስጠራት እንደቻሉ አስታውሰው ውጤቱን ለማስቀጠል እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
የሕግ ት/ቤት መምህርና የክርክር መድረኩ ዳኛ መ/ር እምሻው ተሾመ ከሁለቱም ወገን በቀረቡ ሃሳቦች አሸናፊና ተሸናፊን ከመለየት ባሻገር ጥሩ ዕውቀት እንደተሸመተባቸው ገልጸዋል፡፡ ከታች ያሉ ቀጣይ ተማሪዎችም ይህን ልምድ ማዳበርና ማስቀጠል እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ተከራካሪዎቹ ተቀራራቢ ውጤት ያመጡ ሲሆን በውድድሩ የተሻለ ውጤት ላመጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ገንዘብና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት