የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት ከተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒትና የወንጀል ጽ/ቤት በተገኘ ሰባ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓትን ለማሻሻል እንዲሁም የፍትሕና የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ ያለመ የትብብር ፕሮጀክት ሚያዝያ 25/2017 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ስምንት ዞኖች ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው እንደ ሀገር የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው ከተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ ይህን ዓላማ ለማሰካት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት ጋር ጠንካራ ተቋማዊ ትስስርና ትብብር በመፍጠር አበረታች ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይፋ የተደረገው የትብብር ፕሮጀክት የዚሁ ሥራ መገለጫ ነው ያሉት ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት በፍትሕ ዘርፍ የሚያደርገውን ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያጠናክር በንግግራቸው አረጋግጠዋል፡፡ ፍትሕ ለአንድ ሀገር እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ያወሱት ም/ፕሬዝደንቱ ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው በነጻ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ከፍ ከማድረግ አንጻር የጎላ ሚና ያለው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የተለያዩ አገልግሎቶችን በስፋት እየሰጠ መሆኑን ገለጸው በተለያዩ አካባቢዎች በሕግ ት/ቤት በኩል ባቋቋማቸው የነጻ ሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ማዕከላቱ በርካታ አቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፍትሕ እንዲያገኙ ረድተዋል ያሉት ዶ/ር ቶሌራ ሥራው ከዚህ በተሻለ መንገድ እንዲሰጥ መሰል የትብብር ፕሮጀክቶች ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሕግ ት/ክፍል ኃላፊና የት/ቤቱ ተወካይ ዲን መ/ር አብርሃም ክንፈ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ዞኖች በዩኒቨርሲቲው መደበኛ በጀት እንዲሁም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የነጻ ሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም ለፍትሕ ተደራሽነት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በዋናነት በወንጀል ፍትሕ ላይ አተኩሮ የሚሠራ መሆኑን የገለጹት መ/ር አብርሃም የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ እንዲሁም ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ማለትም ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ ተፈናቃዮች እና የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች የፕሮጀክቱ ዋነኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ጌትነት ደባልቄ በበኩላቸው የትብብር ፕሮጀክቱ በወንጀል ፍትሕህ ሥርዓት ውስጥ የነጻ ሕግ ድጋፍ ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የሚሠራ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙት ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ጋርዱላ፣ ቡርጂ፣ አሌ፣ ኮሬ እና ባስኬቶ ዞኖች ተግባራዊ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት 10 ተጨማሪ የነጻ ሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ለ16 ወራት ያህል በፕሮጀክቱ የሚደገፉ ሲሆን ይህም ዩኒቨርሲቲው ያሉትን የነጻ ሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ቁጥርን 25 እንደሚያደርስ መ/ር ደባልቄ ገልጸዋል፡፡ ጥብቅና፣ ማማከር፣ የሰነድ ዝግጅት እና ሌሎች አግልግሎቶች በማዕከላቱ የሚሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት አቶ አንዱዓለም አምባዬ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ለረዥም ጊዜያት የነጻ ሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም ማኅበረሰቡን እያገለገለ መሆኑ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸው ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ፍትሕን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና ያለውና የፍትሕ ዘርፉንም የሚያግዝ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የወንጀል ፍትሕህ ሥርዓት በኢትዮጵያ እና የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ምንነትና መርሆች ዙሪያ አጭር ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚሆንባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የስምንቱ ዞኖች የፍትሕ እና ፍ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም በማዕከላቱ የሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት