የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት በ2017 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው ለመጡ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከኅዳር 12-13/2017 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት ሥልጠናው በሥርዓተ ጾታ ምንነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በማስወገድ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ እንዲመሩ እና ዓላማቸውን ከግብ እንዲያደርሱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ ነው፡፡ ወ/ሪት ሠናይት ሴት ተማሪዎች ከወንዶች እኩል ጠንክረው በመሥራት በትምህርትና በማኅበራዊ ግንኙነት ውጤታማ መሆን የሚችሉ ሲሆን በተለይ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት መሰል ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ከአሰልጣኞች መካከል የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ዘበነ ተምትሜ በየዓመቱ አዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚገቡ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት ማስገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው የአጠናን ዘዴ፣ የአቻ ግፊት መንስኤዎችና ውጤቱ፣ ራስን መውደድና መንከባከብ፣ የእችላለሁ ባይነት መንፈስን ማዳበር፣ የጭንቀት መንስኤዎችና ውጤቱ፣ ከሌሎች ጋር የሚኖር መስተጋብር፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ያልተፈለገ እርግዝና መንስኤዎችና ውጤቱ እና ሌሎችም ሥልጠናው ከተሰጠባቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው አሰልጣኝ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርት አይናለም መንቾ በበኩላቸው በተለይ ሴት ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን ተጽዕኖዎች እንዲሁም የአቻ ግፊትን መቋቋምና መከላከል እንዲችሉና ለዓላማቸው ተገዢ እንዲሆኑ መሰል ሥልጠናዎች ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊ ተማሪ ኤልሳቤጥ ጌታሁን አዲስ ገቢ ተማሪ እንደመሆናችን ቀደም ተብሎ ሥልጠናው መሰጠቱ በዩኒቨርሲቲው ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት እንድናውቅ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የሚገጥሙንን ችግሮች እንዴት ማለፍ እንዳለብን ግንዛቤ ያገኘንበት ነው ብላለች፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት