የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማእከል "Mainstreaming Integrated Malaria and Neglected Tropical Diseases (NTDs) Campaign System, South Ethiopia" በሚል ርእስ የሚሠራ የምርምር ፕሮጀክት የካቲት 6/2018 ዓ/ም ይፋ አድርጓል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የምርምር ዩኒቨርሲቲነት ግቡን ለማሳካት ሀገራዊ ቅድሚያ በሚሰጣቸውና የማኅበረሰቡን ችግር ተደራሽ በሚያደርጉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥራት ያላቸው ምርምሮችን ለማከናወን እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የትብብር ፕሮጀክቶችን ከመሥራትና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ከማሳተመም ባለፈ ወደ ማኅበረሰቡ አውርዶ በመተግበር ቀዳሚውን ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የጥረቱ አንድ ማሳያ የሚሆኘው ይህ ፕሮጀክትም ወባ እና የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ የተቀናጀ ጥናት በማከናወን ከዩኒቨርሲቲው ራእይ ጋር አብሮ የሚሄድ፣ እንደ ሀገር በሽታዎቹን ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ በእጅጉ የሚደግፍ እና ጠቃሚ መረጃዎችን በማቀበል ለጤና ሥርዓቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል።
የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ወባን እና የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን አስመልክቶ በርካታ ምርምሮችን ማከናወኑን አስታውሰው የአሁኑ ፕሮጀክት ሁለቱን በማጣመር የሚሠራ መሆኑ እና አካቶ ትግበራን ማቀዱ ለየት ያደርገዋል ብለዋል። ፕሮጀክቱ ከሀገር አቀፍ አሁናዊ የትኩረት አቅጣጫ ጋር የሚስማማና በርካታ ባለድርሻዎችን የሚያሳትፍ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ለመሰል ፕሮጀክቶችና የትብብር ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
በ"Task force for Global Health" ዓለም አቀፍ ድርጅት የአፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር እና ከማእከሉ መሥራቾች አንዱ የሆኑት የፕሮጀክቱ መሪ ተመራማሪ ዶ/ር ተሾመ ገብሬ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የወባ እና የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ዘመቻን በተቀናጀ መልኩ በነባሩ የጤና ሥርዓት ውስጥ አካቶ መሥራት ላይ ያተኮረ ሲሆን በደቡብ ኢትዮጵያ የተመረጡ አካባቢዎች የሚተገበር ነው። ከ"Global Institute for Disease Elimination" በተገኘ 200 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት የሁለት ዓመታት ቆይታ ያለው መሆኑንም ደ/ር ተሾመ ተናግረዋል።
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ኮሌጁ አካዳሚክና የምርሞር ሥራዎችን በላቀ መልኩ ለማከናወን የሚያበረታታ ከባቢን ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ተናግረው በዚህም በርካታ መምህራንና ተመራማሪዎች የትብብር ፕሮጀክቶችን ለማምጣት ተነሣሽነቱ ያላቸው ናቸው ብለዋል። ይህ ፕሮጀክትም የተነሣሽነቱ ማሳያና አንዱ ፍሬ ነው ያሉት ዶ/ር ደስታ ላስገኙት አካላት ምስጋናና አድናቆታቸውን ችረዋል። ለፕሮጀክቱ ስኬትም ሆነ ለቀጣይ የትብብር ሥራዎች ኮሌጁ በሙሉ ኃይሉ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባና የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ"CDT-Africa" የቴክኒክ አማካሪ ዶ/ር ዐሥራት መንግሥቴ እና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተመራማሪ እና የጤና ምርምርና ኢኖቬሽን ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዘለቀ መኮንን ለማእከሉም ሆነ ለፕሮጀክት ትግበራው ግብአት የሚሆኑ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦችን አጋርተዋል። ፕሮጀክቱ የትግበራ ጊዜው አጭር እንደመሆኑ ከወዲሁ አብረው የሚሄዱ የጎንዮሽ ፕሮጀክቶችን በማፈላለግና የማእከሉን አቅም በማጎልበት ለቀጣይነቱ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት የሰጡ ሲሆን ከማእከሉ ጋር በሁለንተናዊ መልኩ ተባብረው ለመሥራት እና አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ፣ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ "IMC International"፣ "Carter Center"፣ Orbis International" እና የጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች የጤና መምሪያ ተወካዮች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የመጡና የዩኒቨርሲቲው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





