የ97 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ተማሪ ማኖ መገሶ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ - አባያ ካምፓስ የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሀገር አቀፍ  ፈተና እየወሰዱ ናቸው።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ከቦንኬ  ወረዳ  ካቻሶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የመጡት በዩኒቨርሲቲው የ12ኛ ክፍል የማኅበራዊ ሳይንስ ማጠቃለያ ፈተና ተፈታኙ የ97 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ተማሪ ማኖ መገሶ ትምህርትን ለመማር ብርታትና የዓላማ ጽናት አስፈላጊ መሆኑንና የዕድሜ መጨመር  ከመማር የሚያግድ አለመሆኑን ገልጸዋል። ባሳለፉት ዘመን ለትምህርት የነበራቸው ከፍተኛ ጉጉትና መነሳሳት  እንዲሁም ቁጭት አሁን ላይ ለመማር  ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል። 

"በዕድሜየ ትምህርትን የመማርና የተሻለ ደረጃ የመድረስ ፍላጎቱ የነበረኝ ቢሆንም በሕይወቴ በገጠሙኝ ፈተናዎች ምክንያት ላሳካው አልቻልኩም" ያሉት በተለያዩ ትላልቅ መንግስታዊ ተቋማት የሚሰሩ ልጆች አባት የሆኑት አዛውንቱ ለሀገር እድገት፣ ለነገ አዲስና የተሻለ ኑሮ ትውልዱ ጽናትን ከእኔ ሊማር ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በቀጣይ ትምህርታቸውን የመቀጠል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ተማሪው ውጤት የሚሳካላቸው ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንደሚማሩና እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የመማር ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው  ላደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን ያቀረቡት ተፈታኙ በእስከ አሁን የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደስታኛ  መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በኮሌጁ የመጀመሪያው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር የማኅበራዊ ሳይንስ ማጠቃለያ ፈተና በተያዘለት መርሐ ግብር እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። 

"የ 97 ዓመቱ እድሜ ባለጸጋ አዛውንት ፈተና ሲወስዱ ማየት ሂደቱን የተለየ እና አስደናቂ ያደርገዋል" ያሉት ዶ/ር ስምዖን ትምህርት በዕድሜ የሚገደብ አለመሆኑን ለማስረዳት ጥሩ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት