አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ-አይዩሲ (AMU-IUC) በፕሮጀክቱ ንዑሳን ፕሮጀክቶች የ3ኛ ዲግሪ ጥናቶቻቸውን ለሚሠሩ ተመራማሪዎች አዲስ ባስመጣው በ‹‹Matrice 300 RTK›› ድሮን አጠቃቀም ላይ ከመስከረም 06-10/2017 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት ዘመናዊ ድሮኑ በ“AMU IUC” ፕሮጀክት የፕሮጀክት VI አማካኝነት የተገኘ ሲሆን ቴክኖሎጂው ዩኒቨርሲቲው በአካባቢ ጥበቃ እና መልሶ ማልማት ላይ ለሚያከናውናቸው ጥናቶች የመረጃ አሰባሰብን ትክክለኛነት እና ቅልጥፍናን ከማሻሻል ባለፈ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ከፍተኛ ደረጃና ጥራት ያለው ጥናትና ምርምር ለማድረግ ያለውን አቅም የሚያሳድግ ነው፡፡ የድሮን ቴክኖሎጂው እንደ አጠቃላይ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ለአካባቢው ጥሩ ግብአት ነው ያሉት ዶ/ር ፋሲል በተለይም ለአካባቢ መልሶ ማልት ጥናት፣ የተለያዩ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ውጤታማነታቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ለመሰነድ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን ለማሳመን ይጠቅማል ብለዋል፡፡
ከቤልጂዬም ‹‹Ghent University›› የመጡት አሠልጣኝ ፕ/ር ውተር ሜስ/Prof. Wouter Maes/ ሥልጠና የሰጡበት ድሮን ከቀደሙ ድሮኖች በእጅጉ የላቀ አቅምና የመረጃ ጥራት ያለው መሆኑን ገልጸው ትልልቅ ምርምሮች ሲካሄዱ መረጃ ለመሰብሰብ የሚወስደውን ጊዜ የሚያሳጥር፣ በሰው ሊደረሱ የማይችሉ አስቸጋሪ ቦታዎች ላይ መሥራት የሚያስችል፣ በተለያዩ የሞገድ ርዝመቶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችን የሚወስዱ ባለብዙ ስፔክትራል (multispectral) ካሜራዎች ያሉት በመሆኑ ተመራማሪዎች አስተማማኝ ዝርዝር መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በየኒቨርሲቲው የውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርትና በ‹‹AMU IUC›› ፕሮጀክት VI በቤልጂዬም ሀገር የ3ኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ የምትገኘው መ/ርት ፌቨን ክንፈ ሪሞት ሴንሲንግ ቴክኖሎጂን በውኃ ሥነ ምኅዳር መጠቀም ላይ ምርምራቸውን እያካሄዱ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአባያ ሐይቅ ወደ ጫሞ ሐይቅ ሞልቶ በሚፈስሰው ውኃ ምክንያት በጫሞ ሐይቅ ላይ እየተከሰተ ያለውን የውኃ ጥራት ችግር መቅረፍና የሐይቁን ጤናማነት መመለስ የምርምሩ ዋና ዓላማ መሆኑን መ/ርት ፌቨን ትገልጻለች፡፡ መ/ርት ፌቨን ምርምሩን ለማካሄድ ከዚህ ቀደም የውኃ ናሙና ተሰብስቦ በላቦራቶሪ የሚታይ ሲሆን ምርምሩ በዘመናዊ ድሮኖች ሲደገፍ የናሙና ውጤቱን የሳታላይት ምስል ጋር በማቀናጀት ሐይቁን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመታደግ ይረዳል ብለዋል፡፡
በሐይቁ ላይ ያለው እንቦጭ አረም ሽፋን ያለበት ደረጃ፣ ሐይቁ አካባቢ ያሉ ግብርና፣ ዓሣ ማጥመድና የመሳሰሉ የሰዎች እንቅስቀሴዎች ያላቸው ተጽዕኖ፣ የሐይቁ ዙሪያ ረግረጋማ ስፍራ ተከልሎ መጠበቁ ያለው በጎ አስተዋጽኦ፣ ከደጋማው ክፍል ያለውን የአፈር መሸርሸር መቆጣጠር ቢቻል በሐይቁ ላይ የሚያመጣውን ለውጥና የመሳሰሉትን መረጃዎች በትክክልና ያለብዙ ድካም ሰብስቦ ለመተንተን ድሮኑ ከፍተኛ ጠቃሜታ እንዳለው ተመራማሪዋ ተናግረዋል፡፡
በ‹‹AMU IUC›› ፕሮጀክት IV የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው መ/ር ይበልጣል ይሁኔ በአካባቢው በሚገኙ ግብአቶች የአፈር መሸርሸርን በተለይም ቦረቦር መሬትን ማከምና መልሶ ማገገም ላይ ያተኮረ ጥናት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ጥናቱ በአብዛኛው በአባያ ሐይቅ ተፋሰስ አካባቢ መሆኑንና ለዚህም ከሙከራዎች በዘለለ የድሮን ቴክኖሎጂን እንደሚጠቀም የተናገረው መ/ር ይበልጣል ቀደም ሲል የሚጠቀምበት ድሮን በመጠን ትንሽና መረጃዎችን ጠቅለል አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል፡፡
እንደ ተመራማሪው ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ቦረቦር መሬትን ማከም በሀገራችን ብዙም ያልተሠራበት ሲሆን አሁን ላይ ሥልጠና የወሰደበት ድሮን በመጠኑ ተለቅ ያለ፣ በተለያዩ ሀገራት ለትልልቅ ኢንደስትሪዎች የሚጠቀሙበትና እያንዳንዱን መረጃ ለይቶ በማሳየት ጊዜ፣ ጉልበትና የገንዘብ ወጪን በመቆጠብ ተአማኒ መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ነው፡፡ የጫሞ ሐይቅን ለአብነት የጠቀሰው ተመራማሪው የሐይቁን የደለል መጠን ለማወቅ ከዚህ ቀደም ሞዴል ይጠቀም እንደነበር አስታውሶ አዲሱ ድሮን የተገጠሙለት ሴንሰሮች የደለሉን መጠንና የውኃውን ጥራት ማሳየት የሚችሉ፣ እንቦጭ አረምን ከሌሎች አረንጓዴ ቅጠሎች የሚለይ (Multi Spectral Band) ያለው እንዲሁም ሐይቁ አካባቢ የሚሠሩ የመልሶ ማልማት ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
“Matrice 300 RTK” ድሮን ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል የሚያነሳ፣ እስከ 55 ደቂቃ የበረራ ጊዜ ያለው፣ የበረራ ቆይታውን አስተማማኝ ለማድረግ ጥንድ ባትሪዎች ያሉት፣ እስከ 2.7 ኪ.ግ ተጨማሪ ሴንሰርና ካሜራ የመሳሰሉትን መሸከም የሚችል እንዲሁም በቀላል ዝናብና መሰል አስቸጋሪ የአየር ጠባይና አካባቢዎች ውስጥ ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት