በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል፣ የገጠር ነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ ሴቶችን በምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚ) ለማብቃት እና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ያለመው ታላቅ የግብርና ልማት ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደ የምክክር መድረክ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ሥራ ጀምሯል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
“She-F.E.R.A. (Moringa): Food and Economic Resilience in Agriculture in Ethiopia” (ሺ-ፈራ) የተሰኘውና ለ36 ወራት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት በጣሊያን መንግሥት ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ በቼስቪ (CESVI) መሪነት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዩዳ ኤን አክሲዮን (Ayuda en Acción) እና ከፖዘቲቭ አክሽን ፎር ዲቨሎፕመንት (PAD) ጋር በመተባበር ይተገበራል። ፕሮጀክቱ በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ እና በጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ ላይ ዘላቂ የሞሪንጋ (ሺ-ፈራ) እሴት ሰንሰለት ልማትን ለመዘርጋት ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 9,287 አራሽ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ ለማድረግና 9 የማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋምና ለማጠናከር አልሟል።
በማስጀመሪያ ወርክሾፑ ላይ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጣለዉ ደሬሳ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የተቀረጸው በአሁኑ ወቅት የአካባቢውን አምራች ማህበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ያሉትን እንደ አየር ንብረት ለውጥ፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የአፈር ለምነት መመናመን እና የምግብ ዋስትና እጥረትን የመሳሰሉ ስር የሰደዱ ችግሮችን በቀጥታ ለመፍታት ታስቦ ነው። ፕሮጀክቱ የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ የሞሪንጋ የግብርና-ደንን (agroforestry) ልምዶች ማስፋፋት፣ የማህበረሰብ የችግኝ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር፣ የአርሶ አደሮች የመስክ ትምህርት ቤቶችንና የኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አቶ ጣለው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከሞሪንጋ ምርት የሚገኘውን ጥቅም ለማላቅ ጠንካራ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ፕሮጀክቱ በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ዴስክ ተወካይ Beatrice Geraci በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአካባቢው ላይ እጅግ ፈታኝ በሆኑት የአፈር መመናመን (degradation) እና የምግብ ዋስትና እጥረት ችግሮች ላይ በቀጥታ ትኩረት ማድረጉ ወሳኝና ወቅታዊ ፋይዳ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ሞሪንጋ እጅግ አስደናቂ የሆነ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የፕሮጀክቱን ተፅዕኖ ማሳደግና ማላቅ እንደሚገባ የገለጹት ተወካይዋ፣ ለዚህም ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ኤጀንሲው በተግባር ላይ የዋሉ ተጨባጭ ውጤቶችን እና የተሻሻለ የምግብ ዋስትና ደረጃን ማየት እንደሚፈልግም ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የግብርና ቢሮን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ትእዛዙ ቶማ፣ ፕሮጀክቱን ወደ ኮንሶና ጋርዱላ አካባቢዎች ላመጡት የፕሮጀክቱ አጋሮችና ለጋሾች ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና ገልጸዋል። የሞሪንጋ ልዩ የአመጋገብ፣ የመድኃኒትነት፣ የሥነ-ምህዳር (ኢኮሎጂ)፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ 'ተአምራዊ ዛፍ' ተብሎ እንደሚጠራ የገለጹት አቶ ትዕዛዙ፣ ይህንን ዛፍ ለማልማትና ለመጠቀም የሚመጡ ማናቸውም ሥራዎች በክልሉ መንግሥት እና በግብርና ቢሮው ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍና አቀባበል እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ መሪ እና የፕሮጀክት ዝግጅት ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ በበኩላቸው፤ ይህ ተነሳሽነት በሞሪንጋ እሴት ሰንሰለት አማካኝነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት እና ዘላቂ የግብርና ሽግግርን ለማምጣት ያለውን ስልታዊ አስፈላጊነት በሰፊው አብራርተዋል። ዶ/ር አዲሱ በደቡብ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስተባባሪነት እየለማ ስላለውና በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በዘይሴ ወዘቃ ስለተገነባው የሺ-ፈራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በሰጡት ማብራሪያ፤ የማቀነባበሪያ ፋብሪካው ግንባታ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ እየተጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡ በይፋ ይመረቃል ብለዋል። ይህ ዘመናዊ ተቋም ለሞሪንጋ ምርት እሴት መጨመር እና ለግብርና-ማቀነባበር (agro-processing) ዘርፍ እንደ አንድ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ በኮንሶ እና በደራሼ ወረዳዎች ላይ ለሚቋቋሙት መሰል ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዞች እንደ ዋና ሞዴል እና ተግባራዊ ማሳያ ጣቢያ (demonstration site) ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
የ"ሺ-ፈራ" ፕሮጀክት ሌላው መሰረታዊ ትኩረት የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን በተግባር ማረጋገጥ ነው። በዚህም መሰረት በፕሮጀክቱ በቀጥታ ተጠቃሚ ከሚሆኑት አርሶ አደሮች መካከል እንዲሁም በሚደገፉት ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ በሚቋቋሙ የአመራር አካላት ላይ ሴቶች ቢያንስ የ50 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ይደረጋል። በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ሳይንሳዊ ምርምርን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን፣ አየር ንብረትን የሚቋቋም ግብርናን፣ እሴት መጨመርን እና የገበያ ልማትን በአንድ ላይ ባቀናጀ ዘመናዊ አካሄዱ፤ በአካባቢው ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለመገንባት፣ ተጨማሪ ገቢ ለማመንጨት፣ አካባቢን ለመጠበቅ እና ሴቶችን በሁሉም መስክ ለማብቃት የጎላ አገራዊና ክልላዊ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የጥበብ ምንጭ!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት


