በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ምስለ ችሎትና ክሊኒካል ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዘጋጅነት በሕግ ተማሪዎች መካከል ጥር 16/2018 ዓ/ም ‹‹Child justice, public security, and human Rights: Balancing State power and Fundamental Freedoms›› በሚል ርእስ የመከራከሪያ ሃሳብ ተዘጋጅቶ የምስለ ችሎት (Moot Court) ውድድር ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝደንት አቶ አድማሱ ዘገየ በሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት በርካታ ሥራ የሚፈልግ እንደመሆኑ የፍትሕ መዛባት፣ የሕግ አወጣጥና አተገባበር ችግር እንዳይኖር የሕግ ተማሪዎች ሚና ጉልህ መሆኑን ተናረው ምስለ ችሎት ውድድርም ተማሪዎቹ ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባሻገር የተግባር ዕውቀት እንዲቀስሙ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
የሕግ ት/ቤት ዲን መ/ር አብርሃም ክንፈ መርሐ ግብሩ የሕግ ባለሙያ ለመሆን ጽኑ ፍላጎት የሚጨምር፣ ከጽሑፍ ጀምሮ ጥሩ ተሳትፎ የነበረበትና በትኩረት የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ት/ቤቱ ቀጣይ ሀገር አቀፍ ምስለ ችሎት ውድድር አዘጋጅ መሆኑን የጠቆሙት ዲኑ ከማዘጋጀቱ ባሻገር አሸናፊ ለመሆን እየተጋን ነው ብለዋል፡፡
የምስለ ችሎትና ክሊኒካል ፕሮግራም ቢሮ አስተባባሪ መ/ር እምሻው ተሾመ እንደገለጹት የመርሐ ግብሩ ዓላማ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲያስደግፉ ማድረግ እንዲሁም የሕግ ት/ቤት ከፍርድ ቤቶች ጋር ትስስር መፍጠር እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ በውድድሩ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ተማሪዎች የቤስት ሚሞሪያል ሽልማት፣ ለጥሩ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ እና ለጽሑፍ አሸናፊ የገንዘብ ሽልማት እንዲሁም በውድድሩ ተሳታፊ ለነበሩ እና ለመርሐ ግብሩ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዕውቅና ሰርተፊኬት መበርከቱን አቶ እምሻው ተናግረዋል፡፡
ውድድሩን በዳኝነት የመሩት የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አቶ ደበበ ገዛኸኝ እና አቶ ሰሎሞን ካይማ ተማሪዎች ከተቋማት ብቁ ባለሙያዎች ሆነው እንዲወጡና ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ ፍትሕ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉ ተማሪዎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው መሰል መርሐ ግብሮች ክሂሎታቸውን እንዲያዳብሩና እርስ በእርስ ለመማመር እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የእለቱ የምስለ ችሎት ውድድር ተሳታፊ የሆኑት ተማሪ ምሳሌ ሰሎሞን እና ተማሪ ዮናስ ሲሳይ በውድድሩ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው የተማርነውን ትምህርት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚቻል ያየንበት ነው ብለዋል፡፡ ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር የመናገር፣ የማማከር፣ የመከራከር፣ ክሶችንና መልሶችን እንዴት መጻፍ እንደሚገባ የተግባር ልምምድ ላይ ጠንክሮ በመሥራት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስችል ተወዳዳሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት




