የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ ቆላማ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ፣ ከባህር ዳርና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ‹‹Drugs for Neglected Diseases initiative (DNDi)›› ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም በተገኘ 167 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጀት የተመደበለት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በሽታን ጫናና ሥርጭትን ለማወቅ እየተደረገ ያለው የምርምር ፕሮጀክት በሽታውን በምርመራ ለማረጋገጥ የሚያስችል የአልትራሳውንድ ማሽን አጠቃቀም ሥልጠና ለከፍተኛ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥልጠናው በአማራ ክልል በሚገኘው የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል የተሰጠ ሲሆን በሥልጠናው ከትግራይ፣ ከአፋር፣ ከአማራ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ፕ/ር ወንድማገኝ እምቢያለ ከአራት ወራት በፊት የምርምር ሥራውን ለመጀመር በመረጃ ሰብሳቢነት የሚሳተፋ ከአራቱ ክልሎች የተወጣጡ የጤና መኮንኖች፣ ነርሶች እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው መረጃ ሰብሳቢዎቹ በበሽታው የተጠረጠሩ ሕሙማን በበሽታው መያዝ አለመያዛቸውን ለማረጋገጥ የአልትራሳውንድ ምርመራ አጠቃቀም ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ከሱዳን ካርቱም ዩኒቨርሲቲ በመጣ የዘርፉ ባለሙያ የተሰጠ መሆኑን ያወሱት ፕ/ር ወንድማገኝ ሥልጠናው ለምርምር ሥራውም ሆነ እንደ ሀገር የበሽታው ሥርጭትና ጫና ለማወቅ ለሚደረገው ጥረት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ ቆላማ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ተባባሪ ተመራማሪና በማዕከሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ በቀለ የምርምር ፕሮጀክቱ በአራት የኢትዮጵያ ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በአፋር፣ በአማራ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ 8 ወረዳዎች ወካይ ናሙና ተወስዶ የቆዳ ስር ፈንገስ /Mycetoma/ በሽታን ጫናና ስርጭትን ማወቅና መሰነድ ዋና ዓላማ አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው የፕሮጀክቱ ሂደት ከአፋር ክልል 40 እና ከአማራ ክልል 4 የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ ተጠርጣሪዎች የተገኙ ሲሆን ከሥልጠናው በኋላ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 40 ያህሉ በተደረገላቸው የአልትራሳውንድ ምርመራ 37ቱ ሕሙማን በሽታው እንዳለባቸው መረጋገጡን ገልፀዋል። ይህም በሽታውን በተንቀሳቃሽ አልተራሳውንድ በቀላሉ መለየት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ጠቀሰው በሽታው ለተገኘባቸው ሕሙማንም መድኃኒት በፕሮጀክቱ የተሰጣቸው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የቆዳ ስር ፈንገስ /Mycetoma/ በዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት ከሚሹ የቆላና ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች መካከል የተመደበ የቆዳ በሽታ ሲሆን በሽታዉ ዝናብ አጠር፣ ቆላና ሐሩራማ በሆኑ አካባቢዎች በብዛት ይገኛል:: በሽታው ከ70 በሚበልጡ እውን ፈንገስ  /Eumycetes/ እና ቅርፀ ብዙ ባክቴሪያ /Actinomycetes/ አማካኝነት የሚከሰት  ሲሆን፣ ባዶ እግር መሄድ፣ ነጠላ ጫማ ብቻ መጫማትና በእሾህ፣ እንጨት ወይም ጋሬጣ መወጋት ለበሽታው የሚዳርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁሟሉ፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት