የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከባሕር ዳርና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ‹‹Drugs for Neglected Diseases initiative (DNDi)›› ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ በሽታ ጫናና ስርጭትን ለማወቅ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተካሔደው የጥናት ውጤት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ፖሊሲ  አውጪዎችና ተመራማሪዎች በተገኙበት የካቲት 7/2018 ዓ/ም ይፋ የማድረጊያ መርሐ ግብር ተካሒዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምርና ትብብር ም/ ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው ጥራት ያለው ምርምር ማካሔድ መቻል በምርምሩ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ በምርምሩ መስክ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተክሉ በሪፎርሙ መሠረት የምርምር ሥራዎች ሸልፍ ላይ የሚቀሩ ሳይሆኑ መሬት ወረደው የማኅበረሰብን ችግር የሚፈቱ፣ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት መሆን የሚችሉና ወደ ገበያ ወጥተው ሀብት የሚያመነጩ እንዲሆኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ በሽታ ጫናና ስርጭትን ለማወቅ ያካሔደው ሀገራዊ ምርምር ውጤት የፖሊሲ ግብአት ሆኖ ማገልገል የሚችልና በሽታው ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን የገልጹት ዶ/ር ተክሉ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ መሰል ተጽእኖ ፈጣሪ ምርምሮችን ማካሔድ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቪ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዘርፈ ብዙ ውጤታማና ችግር ፈቺ ምርምሮችንና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን ባለፉት 10 ዓመታት እያከናወነ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የሚያከናውናቸው የትብብር ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደስታ በቀጣይም ፋይዳቸው ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ተግባራትን ለማከናወን ይተጋል ብለዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሕይወት ሰሎሞን የተዘነጉ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደ ሀገር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ሀገር የተዘነጉ ሐሩራማ አከባቢ በሽታዎች ስትራቴጂክ ፕሮግራም እየተከለሰ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ሕይወት የቆዳ ሥር ፈንገስ/Mycetoma/ን አስመልከቶ የተከናወነው የምርምር ሥራ ውጤት ለፕሮግራሙ ዝግጅት ግብኣት ሆኖ ማገልገል የሚችል በእጅጉ ጠቃሚና ወቅታዊ ጥናት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች የቆዳና አባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት፣ በዓለም ጤና ድርጅት የተዘነጉ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች አማካሪ ቦርድ ም/ሰብሳቢ እና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢያለ የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ በዓለም ጤና ድርጅት የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ተብለው ከተለዩ 21 በሽታዎች መካከል አንዱ ቢሆንም በኢትዮጵያ የበሽታውን ስርጭትም ሆነ ጫና የተመለከተ ምንም ዓይነት መረጃ የሌላ መሆኑ የምርምር ፕሮጀክቱን ለመሥራት ያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሽታው በዋናነት እግር ላይ የሚከሰትና በሂደት አጥንትን ጭምር የሚጎዳ፣ ለእግር መቆረጥ የሚዳርግ፣ የሕክምና ሒደቱም አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የሚፈጅና ከፍተኛ ውጪ የሚጠይቅ እንደሆነ ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

በአራቱ ክልሎች በተደረገው ጥናት 102,073 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በተደረገው የልይታ ሥራ በሽታው በሁሉም ክልሎች የተገኘ መሆኑን ፕ/ር ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡ በማኅበረሰብ ተኮር ልየታ ጥናቱ በአፋር ክልል የበሽታው ሥርጭት ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን የገለጹት ፕ/ር ወንድማገኝ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል ብለዋል፡፡ የጥናቱ መካሔድ በሽታው እንደ ሀገር ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ይረዳል ያሉት ተመራማሪው በተለይ የበሽታው ስርጭትና ጫና መታወቁ በሽታው የሀገሪቱ የተዘነጉ ሐሩራማ በሽታዎች ስትራቴጂክ ፕሮግራም አካል ሆኖ አስፈላጊውን በጀት፣ ሕክምና፣ ምርመራና ግብአት እንዲያገኝ በማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው ትኩረት በሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ተባባሪ ተመራማሪና በፕሮጀክቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ በቀለ በዓለም ጤና ድርጅት የተዘነጉ የቆላና ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ተብለው ከተለዩ 21 በሽታዎች መካከል 50 ከመቶው በቆዳ ላይ የሚከስቱ/የሚገለጹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በቆዳ ላይ የሚገለጹ እነዚህ በሽታዎች ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ያላገኙና ይበልጥ የተዘነጉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዓለማየሁ ይህንን ችግር መነሻ በማድረግ እንደ መድኃኒት እደላ ካሉ ሌሎች ፕሮግራሞች ጋር በማቀናጀት በሽታዎቹን የመለየት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ዓለማየሁ ገለጻ በጋጮ ባባ ወረዳ በእከክ መድኃኒት እደላ ወቀት በተሠራው የልየታ ሥራ ከተሳተፉ 4,068 ሰዎች መካከል 2,477ቱ ላይ በትንሹ አንድ በቆዳ ላይ የሚገለጽ የሐሩራማ አካባቢ በሽታ የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸው ይህም በምን ያህል ደረጃ በሽታው የተንሰራፋ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ ጥናት ጋር በማቀናጀት እነዚህን በሽታዎች የመለየት ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ዓለማየሁ ቤት ለቤት በተደረገው የልየታ ሥራ ከተሳተፉ 1ዐ2, 093 ሰዎች ውስጥ 897ቱ ላይ በትንሹ አንድ በቆዳ ላይ የሚገለጽ ሐሩራማ በሽታ ሲገኝባቸው 17.7 ከመቶ የሚሆኑት ላይ ደግሞ ሁለት በቆዳ የሚገለጹ ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ተገኝቶባቸዋል፡፡ እነዚህ የጥናት ውጤቶች ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎችን ከሌሎች ተግባራት ጋር በማቀናጀት መለየት እንደሚቻል ትምህርት የተወሰደበት ሲሆን የተገኙት መረጃዎች በሽታዎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚሠሩ ሥራዎች ግብአት ሆነው የሚያገለግሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቆዳ ሥር ፈንገስ /Mycetoma/ ዝናብ አጠር፣ ቆላና ሐሩራማ በሆኑ አካባቢዎች በብዛት የሚገኝ ሲሆን ባዶ እግር መሄድ፣ ነጠላ ጫማ ብቻ መጫማትና በእሾህ፣ እንጨት ወይም ጋሬጣ መወጋት ለበሽታው የሚዳርጉ ምክንያቶች መሆናቸው በእለቱ ተጠቅሷል፡፡ 

በመርሐ ግብሩ ማጠቃላይ ላይ በጥናቱ ለተሳተፉ ተመራማሪዎች፣ አስተባባሪዎችና ክልሎች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል::

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት