በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማእከል ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ተላላፊ የሆነ የዝሆኔ በሽታ/Lymphatic Filariasis/ ማጥፊያ ማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላን አስመልክቶ ከመስከረም 19-20/2018 ዓ/ም ለባለድርሻ አካላት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በጤና ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ዴስክ ተላላፊ የሆነና ተላላፊ ያልሆነ ዝሆኔ በሽታ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መርጋ መኮንን ተላላፊ የሆነ የዝሆኔ በሽታ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ112 ወረዳዎች እንደሚገኝና በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቀናጀ የበሽታ ዳሰሳ፣ ምርመራና ሕክምና እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላ በዋናነት የሚሠራባቸው ሁለት ዘርፎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በወረዳዎቹ መድኃኒት እደላውን ተከትሎ በተለያዩ ዙሮች ተከታታይ የዳሰሳና የበሽታ ቅኝት ጥናቶችን በማድረግ የዓለም የጤና ድርጅት ስታንዳርዱን ሲያሟሉ መድኃኒት እደላው የሚቆም መሆኑን አቶ መርጋ ገልጸዋል፡፡ ቦረዳ ወረዳ በሽታው በስፋት ከሚገኝባቸው ወረዳዎች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው በወረዳው ማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላ ሲካሄድ ቆይቶ የመጣውን ለውጥ ለማየት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት አፈጻጸሙ ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ በወረዳው ዳግም የመድኃኒት እደላ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ፕሮግራም ማኔጀር አቶ በላቸው ቦክቾ እንደገለጹት ተላላፊ የሆነ የዝሆኔ በሽታ በወባ ትንኝ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን እግርና ሌሎች የአካል ክፍሎችን በማሳበጥ ከፍተኛ የጤና፣ የሥነ ልቦና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትልነው፡፡ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ፣ ጎፋ፣ አሪ፣ ጌዴኦ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ ዞኖች ባሉ 17 ወረዳዎች የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላ እየተካሄደ የቆየ ሲሆን በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጦ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የበሽታዉ ጫና በመቀንሱ ለታማሚዎች ሕክምና እና እንክብካቤ ሥራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሮግራም ማኔጀሩ በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ በሽታው ስለመኖሩ በጥናት ተረጋግጦ ላለፉት 5 ዓመታት ማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ከመድኃኒት እደላ በኋላ በሚደረግ የማረጋገጫ ጥናት የበሽታው ጫና መቀነስ ከ1 በመቶ በታች መሆን ቢገባውም በወረዳው የታየው ውጤት ግን ከተቀመጠው ስታንዳርድ በታች ነው፡፡ በመሆኑም በወረዳው በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ መድኃኒት እደላውን ለማካሄድ ለዞን እና ለወረዳዉ አመራሮችና አስፈጻሚ ባለሙዎች የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የአሠልጣኞች ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማእከል በተለያዩ አካባቢዎች ጥናቶችን በማድረግ እንዲሁም ማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት እደላ ከተካሄደ በኋላ አገልግሎቱ በትክክል ወደ ኅብረተሰቡ መድረሱን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ድጋፋዊ ክትትል በማከናወን ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን አቶ በላቸው ተናግረዋል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ እና የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ዋናቃ ፕሮግራሙን ሲያጠቃልሉ በማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ስርጭትም ሆነ በእግር እብጠት ሕክምና በተግባር በመስክ ምልከታ የታዩ ጉዳዮች ከወትሮ በተሻለ መንገድ በትብብር መሠራት የሚሹ በመሆኑ የሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በወረዳው የእግር እብጠት ቁርጭብትን በቀዶ ጥገና ለማስወገድ ፕሮጀክት ቀርጸው ከዩኒቨርሲቲው ተመራመሪዎች እና ‹‹NaPAN›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመሆን አገልግሎት ላስጀመሩት ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እንቢአለ በመድረኩ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማእከል ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል ማእከሉ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልሉ ጤና ቢሮና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዝሆኔ በሽታን አስመልክቶ ተላላፊ በሆነውና ተላላፊ ባልሆነው የዝሆኔ በሽታ በተለያዩ ወረዳዎች ፕሮጀክቶች መተግበራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ለባለሙያዎችና ለጤና አመራሮች ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ትግበራውን በመከታተልና የዳሰሳ ጥናቶችን በማካሄድ ማእከሉ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡ ከመድኃኒት እደላ ዘመቻው ጎን ለጎን ለታማሚዎች ሕክምና፣ የኢኮኖሚ ድጋፍ፣ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት አቅም መፍጠር፣ ግንዛቤ ማስጨበጥና ሌሎችም ድጋፎች የሚደረጉ ሲሆን በዚህ ረገድ ከዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
የማእከሉ ተመራማሪ ዓለማየሁ በቀለ በማእከሉ ከዚህ ቀደም በሽታውን አስመልክቶ የተለያዩ ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን በበሽታው ምክንያት በተለይ ተላላፊ ባልሆነው ዝሆኔ የሚመጣውን የእግር እብጠት ላይ የሚፈጠረዉን ቁርጭብት/Nodule/ በመለስተኛ ቀዶ ጥገና በማስወገድ እግራቸው መጠኑ ቀንሶ ጫማ ማድረግና መንቀሳቀስ እንዲችሉ መደረጉን በዚህም ከ80 በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ማእከሉ የመጀመሪያ ደረጃ ክብካቤ አሃድ ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የቆዳ ሐሩራማ በሽታዎች ሕክምና ወደታችኛዉ የጤና መዋቅር እንዲወርድ ጉልህ ሚና እየተጨወተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በዓለም የጤና ድርጅት ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች አስተባባሪ ዶ/ር ንጉሥ ማናየን ጨምሮ ከጤና ሚኒስቴርና ከክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከዞንና የወረዳ አስተዳደሮች፣ ከዩኒቨርሲቲው እንዲሁም ከቦረዳ ወረዳ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት