የደቡብ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሐምሌ 19/2017 ዓ/ም በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ከፍተኛ ውድመት ለደረሰበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ /ኦቶና / ሆስፒታል ነሐሴ 3/2017 ዓ/ም 6 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

 የፎረሙ  አባል ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በቦታው በመገኘት በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሐዘን የገለፁ ሲሆን ለሆስፒታሉ መልሶ መቋቋምና ማስጀመሪያ የሚሆን ወደ 6 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ  ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ አዳዲስ የታካሚ አልጋዎች፣ ዊልቸሮች፣ ክራንቾች፣ ማይክሮስኮፖች፣ ፍራሾችና የተለያዩ መድሃኒቶችና የሕክምና ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።

ፎረሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ኃብትና አቅማቸውን በማቀናጀት በተናጠል የሚያከናውኗቸውን ፈርጀ ብዙ ተግባራት በጋራ በመሥራት ማኅበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ታስቦ መቋቋሙ ይታወቃል። አርባ ምንጭ፣ ዲላ፣ እና ጂንካ የዩኒቨርሲቲዎች ድጋፉን ያደረጉ የፎረሙ አባል ተቋማት ናቸው ።

የፎረሙ ሰብሳቢና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል ሆስፒታሉ ለረዥም ዓመታት የክልሉን ሕዘብ ሲያገለግል የቆየ ባለውለታ መሆኑንና በቅርቡ በደረሰበት የእሳት አደጋ በሆስፒታሉ ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። በአጭር ጊዜ አስፈላጊው እደሳት ተደርጎለትና ቁሳቁሶች ተሟልተውለት ወደ ሥራ በመመለስ አገልግሎቱን ለሕዝቡ መስጠት እንዲችል ለማገዝ ታስቦ ይህ የመጀመርያ ዙር  ድጋፍ መደረጉን ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ ከቀድሞ ቁመናው በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክትም ፕሬዘደንቱ ጠይቀዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኤልያስ ዓለሙ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዝደንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ ሆስፒታልን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ማቋቋም ብዙ ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውሰጥ ሆስፒታሉ ወደ አገልግሎት እንዲገባና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲጀምር ለማስቻል ታስቦ ፎረሙ ድጋፉን ያደረገ መሆኑን ተናገረዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር  ጉቼ ጉሌ  ይህ ችግር በደረሰብን ወቅት ከጎናችን በመቆም ሆስፒታሉ የወደመበትን ንብረቶች በመተካት ወደ ሥራ ለመመለስ በዩኒቨርሲቲዎቹ  የተደረገው ድጋፍ እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት