በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ አማካሪዎች 1ኛ ዙር ዓለም ዓቀፍ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከኅዳር 1-2/2017 ዓ/ም ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በጅማና በቤልጅየሙ ‹‹Ghent›› ዩኒቨርሲቲ ትብብር እንዲሁም በ ‹‹VLIR-UOS›› የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራው ‹‹Ethiopian SuperStars›› የተሰኘ ፕሮጀክት ሥራ አካል ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በቂ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ እና ለትምህርት ጥራት መሻሻል ጉልህ ሚና የሚያበረክቱ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ቁጥር ከማሳደግ አንጻር መሥራት እንደሚጠበቅ ሀገራዊ የምርምር ውጤቶች የሚያመላክቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ እ.ኤ.አ በ2023 የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ ሰባት በመቶ ለማሳደግ ቢታቀድም ቁጥሩ ከአንድ መቶኛ ሊሻገር አልቻለም፡፡ በመሆኑም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መሰል ሥልጠናዎች በትብብር መዘጋጀታቸው የአማካሪዎችን አቅም ከማሻሻል አንጻር የላቀ ሚና እንደሚኖረው ዶ/ር ዓለማየሁ አመላክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ድኅረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በሀገሪቱ ሥርዓተ ትምህርት ልክ ትምህርታቸውን በመከታተል አለመጨረሳቸው እንዲሁም በተማሪዎች፣ በመምህራን እና በአማካሪዎች መካከል ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የተካሄዱ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን ጉዞ የድኅረ ምረቃው ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ ይወጣል ያሉት ዶ/ር ተክሉ ሥልጠናው ዘርፉን ለማጠናከርና የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የአማካሪዎችን አቅም ለማጎልበት ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጡት አሠልጣኞች ዶ/ር መልሰው ደጀኔ እና ዶ/ር ብሩክ ብርሃኑ እንደገለጹት በሀገር ደረጃ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች በጥራት እና በቁጥር የተሻለ ደረጃ ላይ አለመገኘታቸውን እንዲሁም አማካሪዎች ለተማሪዎች መማር ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር ጉድለቶች እንደሚታይባቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አማካሪ መምህራን የተማሪዎችን ልዩነቶችና ፍላጎቶች በመገንዘብ የተሻሉ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማፍራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ እና ዶ/ር ደረጀ ጸጋዬ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የሚያማክሩ መምህራን ላይ የተሻለ አቅም የሚፈጥር እንዲሁም በተማሪዎችና በአማካሪዎች መካከል የሚኖረው ቀረቤታ ምን መምሰል እንደሚገባው እና የተማሪዎች፣ የአማካሪዎችና የዩኒቨርሲቲውን ድርሻ አስመልክቶ አቅጣጫ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናው ከአዲስ አበባ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች በመቀጠል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ በባሕር ዳር፣ መቐለ፣ ሀዋሳ እና አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት መረጃ እንደሚያመላክተው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 330 የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን በሥልጠናው ከሁሉም ኮሌጆች በመመልመያ መስፈርቶች ተቀባይነት ያገኙ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የሚያማክሩ 12 አማካሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት