ፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ ማስተማር ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ ማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም ከሕንዱ አንድህራ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ፕ/ር ጳውሎስ ከማስተማር ሥራቸው በተጨማሪ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ፋከልቲ ዲንና ተባባሪ ሬጂስትራር፣ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር፣ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና ምክትል ዲን በመሆን እንዲሁም በተለያዩ ሙያዊና የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ላበረከቱት አስተዋጽዖም ከተማሪዎች ኅብረት የወርቅ ቀለበት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ሁለት ጊዜ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ፕ/ር ጳውሎስ በምርምሩ መስክም የራሳቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ 44 የምርምር ጽሑፎችን በታዋቂ ጆርናሎች ላይ ያሳተሙት ፕ/ር ጳውሎስ በ12 የምርምር ኮንፍረንሶች ላይም ምርምሮቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በሕንዱ አንድህራ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ‹‹Recent Trends and Future Perspectives in Material Science›› የተሰኘ ሲምፖዚየም በላቀ ምርምርና አቀራረብ ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡
ፕ/ር ጳውሎስ የPSARJ /Pharmaceutical Sciences & Analytical Research Journal/ ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል፣ የEJSSD /Ethiopian Journal of Science and Sustainable Development/ አማካሪ ቦርድ አባል እና የOIJS /OMO International Journal of Sciences/ ተባባሪ አርታኢ ሆነው የአካዳሚኩን ማኅበረሰብ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፊዚክስ እና በማቴሪያል ሳይንስና ምኅንድስና የትምህርት መስኮች 65 የማስተርስ ተማሪዎችን በማማከር ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን እንዲያጠናቅቁ አድርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፕ/ር ጳውሎስ በማቴሪያል ፊዚክስ የትምህርት ዘርፍ የሚማሩ ሰባት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን የምርምር ሥራዎች አማካሪ በመሆን እየሠሩ ሲሆን የተለያዩ ኮርሶችን ለሁለተኛና ለሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በመስጠት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛል፡፡ ፕ/ር ጳውሎስ የዶክትሬት ተማሪዎቻቸው የላቀ የምርምር መሣሪያዎችን፣ ግብአቶችን እንዲሁም ጠቃሚ የምርምር ዕድሎችን እንዲጠቀሙ ለማስቻል በተለያዩ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ከሚሠሩ ፕሮፌሰሮች ጋር ዓለም አቀፍ ትብብር በመፍጠር ለተማሪዎች መልካም ዕድልም ፈጥረዋል።
ፕ/ር ጳውሎስ በእስከአሁን ቆይታቸው በመማር ማስተማር፣ በምርምር እንዲሁም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ዩኒቨርሲቲውን በትጋት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ከታኅሣሥ 1/2017 ዓ/ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ሆነው በውክልና እንዲያገለግሉ መድቧቸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት