በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምኅንድስ እና ሂሳብ ማዕከል (STEM Center) አስተባባሪነት በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ የተመረጡ 2 ደረጃ ት/ቤቶችና ከጋሞ ባይራ ሞዴል አዳሪ 2 ደረጃ ት/ቤት ለተወጣጡ ተማሪዎች ፊዚክስ ትምህርትንና ‹‹National Aeronautics and Space Administration/NASA(ናሳ)ን አስመልክቶ ግንቦት 16/2016 ዓ/ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውን ከናሳ ጆንሰን የሕዋ ማዕከል/ NASA-Johnson Space Center/ የመጡት ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ ሰጥተዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

አሠልጣኝ ዶ/ር ጥላዬ ታደሰ የሕዋ ዳሰሳ፣ ጥቅሞቹ፣ ተግዳሮቶቹ፣ ወደ ሕዋ የመሄድ ምክንያቶች፣ የሕዋ ጥናት አስፈላጊነት እና በጥናቱ ውስጥ ለሚከሰቱ ተግዳሮቶች መፍትሔ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮችና ከተማሪዎች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡ አሠልጣኙ የሕዋ ምርምርና ዳሰሳ በምድራችን ለሚያገለግሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ብሎም የተፈጥሮ ሀብትን በሚገባ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ለወጣቶች ማሳየትና እንዲነሳሱ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አምሳሉ በአሁኑ ጊዜ ከቀድሞ ይልቅ ምቹ የትምህርት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ተማሪዎች ራዕይን አንግበው በመጓዝ በተለይ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማሳደግ ለተሻለ ውጤት መሥራትና ለትውልድ የሚበቃ ታሪክ ለመሥራት መበርታት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ባይራ ሞዴል አዳሪ 2 ደረጃ ት/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ አበራ ትምህርት ቤቱ ትልቅ ራዕይን ሰንቆ እንደ መመሥረቱ መሰል ፕሮግራሞች በየጊዜው ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ የሕዋ ዳሰሳ፣ ተግዳሮቶችና ጥቅሞች ላይ ገለጻ መደረጉ ተማሪዎችን የናሳ ተመራማሪ ለማድረግ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚፈጥርና ተስፋ የሚታይበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጋሞ ባይራ ሞዴል አዳሪ 2 ደረጃ ት/ቤት የ10 ክፍል ተማሪና ሠልጣኝ ሁለመናው ደፋሩና ተማሪ ቸርነት ግርማ በሰጡት አስተያየት ስለሕዋ ሳይንስ የተደረገው ገለጻ፣ የአሠልጣኙ የሕይወት ተሞክሮና በተማሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽ ብዙ ዕውቀት የገበዩበትና ተነሳሽነትን የጫረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት