ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነባርና የ2018 ዓ/ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ‹‹የአርባ ምንጭ ቃል ኪዳን ቤተሰብ›› አመሠራረትና ቀጣይ ተግባራት ላይ ጥቅምት 21/2018 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የቃል ኪዳን ቤተሰብ ውሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በከተማዋ ተነሳሽነት ተመሥርቶ በመንግሥት በኩል ዕውቅና ያገኘ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይህን በጎ ተሞክሮ ወስዶ በዩኒቨርሲቲው እና በአርባ ምንጭ ከተማ ቤተሰባዊ ትስስር በመፍጠር ተማሪዎቹን በመልካም ሥነ ምግባር ለማነጽና ለመደገፍ ‹‹የአርባ ምንጭ ቃል ኪዳን ቤተሰብ›› መመሥረቱ ተገልጿል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለጹት ስምምነቱ ዩኒቨርሲቲውን ቀዳሚ ምርጫ በማድረግ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመጡ ተማሪዎች እና በአርባ ምንጭ ከተማ ማኀበረሰብ መካከል ቤተሰባዊነትና አብሮነትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በአተገባበሩ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር መርሐ ግብሩ ተዘጋጅቷል፡፡
እንደ ኃላፊዋ በቃል ኪዳን ስምምነቱ መሠረት ተማሪዎች የሌሎችን ቋንቋና እሴቶች ማክበር፣ ከቃል ኪዳን ወላጆች ጋር በስልክ እና በአካል መገናኘት፣ ለመጡበት አካባቢ የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ መማር ማስተማር፣ የከተማውን የተፈጥሮ ገጸ በረከቶችና የሰላም እሴት ማስተዋወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በሌላ በኩል የቃል ኪዳን ወላጆች ከቃል ኪዳን ልጆቻቸው(ተማሪዎቹ) ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር፣ የትምህርት አቀባበልና የሥነ ምግባር ሁኔታቸውን መከታተል እንዲሁም ሀገራዊና ሃይማኖታዊና በዓላትን አብረው ማሳለፍና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎንያስ ፈንቴ ስምምነቱ ለተማሪዎቹ ተጨማሪ ቤተሰብ የሚፈጥር እና ለሀገራዊ ሰላም መጎልበት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግሮ ኅብረቱ ለስምምነቱ ተግባራዊነት በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡
ከአማራና ከሲዳማ ክልሎች የመጡት ተማሪ ሀብታሙ አይቶልኝ እና ተማሪ ቅድስት ገረመው ስምምነቱ ከወላጆቻችን ርቀን ከመምጣታችን ጋር ተያይዞ የሚመክረንና የሚገስጸን ቤተሰብ በቅርብ እንዲኖረን የሚያስችልና የሚደገፍ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ከተማሪዎች ኅብረት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ በተወጣጡ ባለድርሻዎች ትብብር የቃል ኪዳን ቤተሰብ መሆን በሚሹ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና በከተማው ማኀበረሰብ መካከል የትውውቅና የውል ስምምነት መርሐ ግብር የሚካሄድ ይሆናል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

