የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ ተቋም ለማድረግ የሚያስችሉ አስፈላጊ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የሥራ ሪፖርቱን ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል ባቀረበበት ወቅት ገልጿል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የራስ ገዝ አስተዳደር ፕሮጀክት ጽ/ቤት የፕላን፣ የፕሮጀክትና የፕሮግራሞች አስተባባሪ ዶ/ር እንደልቡ ጎአ የሥራ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ራስ ገዝ ተቋም መሆን ማለት ራስን በራስ መምራት ማለት መሆኑን ገልጸው አሠራሩ የራስን መሪ በራስ የመምረጥ፣ አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችን የመክፈትና የመዝጋት እንዲሁም በተለያዩ የኢንቬስትመንት ዘርፎች ላይ የመሳተፍ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማሸጋገር የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን በሪፖርታቸው የገለጹት ዶ/ር እንደልቡ የዩኒቨርሲቲው ነባር መምህራን የተሳተፉበት የራስ ገዝነት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ መሆኑን እንዲሁም የተቋሙን አሁናዊ ሁኔታ ማወቅ የሚያስችል ጥናት (SWOT Analysis) ጨምሮ የዩኒቨርሲቲውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የማዘጋጀትና የተቋሙን የሴኔት መተዳደሪያ ደንብ የመከለስ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ባሻገር ራስ ገዝ ለመሆን የሚረዱ 10 የፖሊሲ ዶክመንቶች እየተዘጋጁ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው የ‹‹Resource Mobilization & Diversification Policy››፣ ‹‹Endowment policy›› ፣ ‹‹Student Admission Policy›› እና ‹‹Alumni Engagement Policy›› የተሰኙ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዶች አስፈላጊውን የውስጥና የውጭ የግምገማ ሂደት አልፈው ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት ለማጸደቅ የቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲውን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር የሚያሻግሩ ቀሪ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ሥራ በጽ/ቤቱ በኩል በትኩረት የሚሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የራስ ገዝነት አስተዳደር ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ይዞ የሚመጣ አሠራር መሆኑን የገለጹት ዶ/ር እንደልቡ በትምህርት ሚኒስቴር የተቀመጡ የራስ ገዝነት አስተዳደር መስፈርቶችን ለማሟላት ለሚደረጉ ጥረቶች መላው የዩኒቨርሲቲው አመራርና ማኅበረሰብ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሪፖርቱን ተከትሉ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነሥተው ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት




