የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ኅዳር 3/2019 ዓ.ም ውይይትና ግምገማ አካሂደዋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ይፍሩ እስከ መስከረም 30/2019 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የሦስት ወራት ዋና ዋና ክንውኖች አቅርበዋል። በሪፖርቱም የመማሪያ ክፍሎች፣ መጸዳጃ ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እድሳት መከናወኑን፣ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለጻ (Orientation) ተሰጥቶ የኮርስ ድልድል መጠናቀቁን እንዲሁም የአርባ ምንጭ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መቋቋሙንና በአባያ ካምፓስ ስታዲየም ስታንዳዱን በማሻሻል የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ እንዲያስተናግድ መደረጉን አብራርተዋል።
አቶ ሰለሞን አክለውም በበጀት ዓመቱ በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ጠቅላላ ቁጥር 21,364 መድረሱን ገልጸው፣ የ"5 ሚሊዮን ኮደርስ" ዕቅድ አፈጻጸምን ከ47 በመቶ ወደ 60 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። በምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍም ወደ 2019 ዓ.ም ከተሸጋገሩ 269 ችግር ፈቺ ምርምሮች መካከል 68ቱ መጠናቀቃቸውን፣ 35 የግራንድ እና 20 የሴቶች ምርምር ፕሮፖዛሎች ጸድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለማሳተም ከታቀዱ 1,000 የምርምር ውጤቶች ውስጥ 210 (21 በመቶ) መታተማቸውን፣ አንድ የፖሊሲ ብሪፍ መውጣቱን፣ ሁለት ዓለም አቀፍ የትብብር ፕሮጀክቶችን በማሸነፍ 54.92 ሚሊዮን ብር የውስጥ ገቢ መገኘቱንና ዘመናዊ የድሮን ሲስተም (Advanced Drone System) መገኘቱን አስታውቀዋል። በቀጣይም ለፕሮግራምና ላብራቶሪ አክሬዲቴሽን፣ ለውስጥ ኦዲት፣ ለሥርዓተ ትምህርት ክለሳ፣ ለመምህራን ብቃት ማሻሻያና ለምርምር ውጤቶች ንግድ ትስስር (Commercialization) ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶክተር ኢንጂነር አብደላ ከማል በበኩላቸው የመማር ማስተማሩን ጥራት ለማረጋገጥ የመምህራን የትምህርት ደረጃ ምጣኔን ማሻሻል፣ የጥራት ኦዲት ማካሄድና የትምህርት ክፍለ ጊዜ መቆጣጠሪያ ዳሽቦርድን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። የሃይብሪድና የኦንላይን ትምህርት አሰጣጥን ማጠናከር፣ የዩኒቨርሲቲውን ድረ-ገጽ ወቅታዊ በማድረግ ተቋማዊ ስኬቶችን፣ ዓለም አቀፍ ህትመቶችንና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። ፕሬዝደንቱ አያይዘውም ባለድርሻ አካላት ለክረምት ተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ መሻሻል በትኩረት እንዲሠሩና በሪፖርቱ ያልተካተቱ ዝርዝር ተግባራት ተሟልተው እንዲቀርቡ መመሪያ ሰጥተዋል።
የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ በስታዲየሙ ላይ የተደረገው የሪፎርም ሥራ የተቋሙን ራስ ገዝነት የሚደግፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በትምህርት ሚኒስቴር በኩልፎ ካምፓስ የተቋቋመው የፌዴራል አዳሪ ትምህርት ቤትና በአባያ ካምፓስ የተገነባው የማህበረሰብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ የሚያጎሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የካውንስል አባላት በግዥ ሥርዓት፣ በመማር ማስተማር ግብዓት አቅርቦትና በሪፖርቱ መካተት በሚገባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን፣ ከመድረኩ መሪዎች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

