አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በምርምር ሥነ ምግባር፣ ዓለም ዓቀፋዊ የምርምር ተሞክሮዎች፣ በምርምር መርሆዎች እንዲሁም በትምህርት ተቋማቱ የምርምር ሥነ ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ እና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከጥር 16-17 2017 ዓ/ም በገጽ ለገጽ እና በበይነ መረብ የታገዘ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሥልጠናው ሀገራዊ የለውጥ ሥራዎች አካል ሲሆን የምርምርን ጥራት ለማሻሻል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን በመከተል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ምርምሮችን እያከናወነ የሚገኝ መሆኑንና የሚከናወኑ ምርምሮች ዓለም አቀፋዊ የምርምር ሥነ ምግባርን የተከተሉ ከማድረግ አንጻር ጠንካራ አሠራር በመዘርጋት እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር ሥነ ምግባር ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር አቡሌ ታከለ እንደገለጹት ሥልጠናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚከናወኑ ምርምሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መሙላት፣ ተመራማሪዎች ዓለም አቀፋዊ የምርምር ዕውቀት እንዲኖራቸው ማስቻል እንዲሁም በትምህርት ተቋማቱ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችን የሚቆጣጠር የምርምር ሥነ ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡
በትምህርት ተቋማቱ የሚከናወኑ የምርምር ተግባራትና የኅትመት ውጤቶችን የሚቆጣጠርና የሚከታተል የምርምር ሥነ ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም የምርምር ጥራትን ለማሻሻልና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን በተሻለ መልኩ ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር አቡሌ ጠቁመዋል፡፡ በመልካም ሥነ ምግባር የተመራ ምርምር ለሰው ልጅ ክብር ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጉዳትና ስጋቶችን ማስቀረት የሚችል እንዲሁም በኃላፊነት የሚመራና የተጠያቂነት ሥርዓት የሚከተል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር ሠራዊት ሃንደሶ በበይነ መረብ በሰጡት ሥልጠና ባለፉት ዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የትምህርት ፕሮግራሞች እየጨመሩ መምጣታቸው በተቋማቱ በርካታ የምርምር ሥራዎች እንዲከናውኑ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የምርምር ጥራትን ለማሻሻል በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የምርምር ሥነ ምግባር ኮሚቴ በቦርድ ደረጃ ተቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ምርምር ለሰዎች እኩልነትና አንድነት ትልቅ ክብር የሚሰጥ፣ የተለያዩ ባህልና ቋንቋ ልዩነቶችን ታሰቢ ያደረገ፣ በመልካም ሥነ ምግባር የሚመራ መሆን እንደሚገባው በሥልጠናው የተመላከተ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ማእከል በማድረግ የደቡብ ክላስተር ተብለው ከተለዩ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ መምህራንና ተመራማሪዎች በሥልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት