አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጥር 29/2018 ዓ/ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 13ኛውን ዓመታዊ የምርምር እና ኅትመት ወርክሾፕ አጠናቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ስድስት ወራት በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ የምርምርና የኀትመት ተግባራት ማከናወን መቻሉንና በዚህም የተመራማሪዎች ብርቱ ጥረት የሚበረታታና ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ተክሉ አያይዘውም ወርክሾፑ በምርምርና በኀትመት ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦች ማስቀጠል የዕውቀትና ምክረ ሐሳብ ልውውጥ የሚካሄድበት ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም አጀንዳዎች አኳያ የትምህርት እና የምርምር ጥራት ለማሻሻል የመመምህራንና የተመራማሪዎችን የትምህርት ደረጃ ለማሳደግ እንዲሁም የምርምር ማዕከላትንና ቤተ ሙከራዎችን ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የምርምር እና የኀትመት አቅም እያደገ መሆኑንና 128 የሚሆኑ የምርምር ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በዩኒቨርሲቲው ተነሣሽነትና የትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫን መሠረት በማድረግ ተመጋጋቢ የሆኑ 10 የምርምር ጭብጦች መለየት፣ የጥናትና ምርምር መተዳደሪያ ሰነድ ማዘጋጀት፣ የምርምር ሥነ ምግባር ኮሚቴ ማቋቋም እና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የትብብር ፕሮጀክቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ኃይሉ የተመራማሪዎችን የትብብር አቅም ለማሻሻል ዓለም አቀፍ የግራንት ፕሮጀክት አጻጻፍ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀትና በማስተባበር፣ ለግራንት ፕሮጀክት አሸናፊዎች እና የተሻለ የኀትመት ሥራ ለሠሩ መምህራንና ተመራማሪዎች ዕውቅና በመስጠት ዳይሬክቶሬቱ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አሸናፊ በዩኒቨርሲቲውና በትብብር የተከናወኑ ፕሮጀክቶችና በትብብር የሚሠሩ ተቋማት ታሪካዊ ዳር የማደራጀት ተግባር መከናወኑንም አክለዋል።
በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ታደሰ የአእምሯዊ ንብረትን አስመልክቶ ባቀረቡት ገለጻ አእምሯዊ ንብረት የሰው ልጅ የአእምሮ እሳቤና የማይዳሰስ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት አባል መሆኗን የገለጹት አቶ ስንታየሁ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው የምርምር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ማስመዝገብ የሚጠበቅበት መሆንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወርክሾፑ 128 ያለቁና 53 በሂደት ላይ ያሉ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የዩኒቨርሲው ጥናትና ምርምር ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና የሌሎች ሥራ ክፍል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





