የዩኒቨርሲቲው ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት ከብርብር ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት እና በብርብር ከተማ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ አምራች ማኅበር ጋር በመተባበር ማዘጋጃ ቤታዊ ኦርጋኒክ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ መቀየርን አስመልክቶ ሰኔ 30/2017 ዓ/ም ወርክሾፕ አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን የሚደግፍና ቆሻሻ ሀብት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው የቆሻሻ አያያዝና የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ አዘገጃጀት ቴክኖሎጂ ማቅረብ፣ ሳይንሳዊና ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ፣ የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ጥራት እና ደኅንነት የምርምር እና ክትትል ሥራዎችን መሥራት የመሳሰሉ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
የ‹‹RUNRES›› ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ፈይሶ የማዘጋጃ ቤታዊ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ የመቀየር ቴክኖሎጂን በብርብር ከተማ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው ሥራው የባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ወርክሾፑ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡ በሃሳብ ደረጃ ያለውን ወደ መሬት በማውረድ ሥራውን ለመጀመር ያለንበትን ደረጃ እንዲረዱና ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ወርክሾፑ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ማዘጋጃ ቤታዊ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚቀይር፣ የሙዝ ምርትን ወደ ዱቄት የሚቀይር እና ዩሪያ ማዳበሪያን ሊተካ የሚችል ከሰው ሽንት የሚሠራ ማዳበሪያ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውን አቶ አባይነህ ጠቁመዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የቢዝነስ ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ በተፈጥሮ ሂደት የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ለመሬት ማዳበሪያነት በመገልገል ቆሻሻን ወደ ገንዘብ እንዴት መቀየር እንደሚቻል አጠር ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የብርብር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ወንድማገኝ ወይዛ ፕሮጀክቱ ወደ ከተማቸው ሲመጣ ከቆሻሻ የጸዳ ከተማ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ በመቀየር ማቅረቡ ለአርሶ አደሩ ትልቅ ዕድል ነውም ብለዋል፡፡
የብርብር ከተማ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ባደገ ባልጣ እንደገለጹት ማኅበሩ በፕሮጀክቱና በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ድጋፍ ከተመሠረተ 2 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ቢሮና ማምረቻ ቦታዎችን ማዘጋጀት፣ አጥር ማሳጠር፣ የመብራትና የውኃ መስመር ዝርጋታ ሥራዎችን በመሥራት ለሥራ ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የከተማውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ወደ መስመር በማስገባትና ጽዱና ውብ ከተማ ለመፍጠር እንደሚሠራ ያወሱት አቶ ባደገ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡
በወርክሾፑ መጨረሻ የብርብር ከተማ አመራሮች እና ተጋባዥ እንግዶች የማኅበሩን የሥራ ቦታ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት