አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ‹‹ኢነርጂ አሲስታንስ/Energy Assistance›› ጋር በመተባበር በጋሞ ዞን ዲታ ወረዳ ጎዛ ቀበሌ በጎዛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በ1.8 ሚሊዮን ብር ወጭ ያሠራው 10 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሰኔ 2/2017 ዓ/ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምራል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ዘመኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ በመሆኑ ፕሮጀክቱ የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማገዙም ባሻገር ለሀገር የሚጠቅሙ ምሁራንን ከማፍራት አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹በጨለማ መካከል ብርሃንን ማየት የመሰለ ነገር የለም›› ያሉት ፕሬዝደንቱ ሥራውን ከስኬት ላደረሱ የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች፣ መኀንዲሶች፣ ለፕሮጀክቱ አጋር አካላት እንዲሁም ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ማኅበረሰቡ ላሳየው ተነሳሽነትና ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምርን መሠረት በማድረግ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ተግባራትን ከምን ጊዜውም በላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ የትምህርትና የጤና ተቋማት ላይ ያለውን የኃይል አቅርቦች ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ በዚህም በርካታ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በሶላር ኃይል የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገለግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የጎዛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ይህን አገልግሎት በማግኘት 45ኛው ተቋም ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም ዩኒቨርሲቲው ምርምርን መሠረት በማድረግ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ተግባራትን ማከናወኑን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ያሊሾ ግርማ ማዕከሉ በፀሐይ፣ በመለስተኛ ወንዝ፣ በከርሰ ምድር እንዲሁም በባዮ ማስ ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን እና ኃይል በማልማት ለማኀበረሰቡ ተጠቃሚነት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ት/ቤቱን የመብራት ተጠቃሚ በማድረግ የመማር ማስተማሩ ሥራ በመረጃና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ የት/ቤቱን ICT ማዕከል በግብዓት በማደራጀት በኩል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በኢነርጂ አሲስታንስ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኢ/ር አሸናፊ ግርማ ድርጅቱ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ፕሮጀክት በዞኑ 5ኛው ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በሚያቀርባቸው በምርምር የተደረገፉ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ ለመሥራት ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ዶሳ ፕሮጀክቱ ለማኅበረሰቡ ብርሃንን ያሳየ እንዲሁም ለመማር ማስተማር ሥራ መሻሻል ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱን በአግባቡ መጠቀም እና ማስተዳደር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ወረዳው የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለ ድርሻ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት