አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በኮሌጁ የ3 ወር አጫጭር ሥልጠና ለሚወስዱ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ ሠልጣኞች የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ ዲዛይን፣ ጥገና እና ዕቅድ ዙሪያ ነሐሴ 2/2017 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ወረዳዎች የፀሐይ ታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂን መዘርጋቱን አስታውሰው ቴክኖሎጂው ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት ሥልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥልጠናው ዋና አስተባባሪ አቶ አስመላሽ ዳኜ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ አድቬንቲስት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን ግብረ ሠናይ ድርጅት እና የአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን በመተባበር ከጀርመን መንግሥት በሚገኝ ድጋፍ የሚሠራ ነው፡፡ የሥልጠናው ዓላማ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው ሥራ የሌላቸው ወጣቶች የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በአርባ ምንጭ፣ ወልቂጤ፣ ድሬ ዳዋ እና አፋር በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ 480 ተማሪዎችን በፀሐይል ኃይል ቴክኖሎጂ አሠልጥኖ ለሥራ ለማብቃት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት የትብብር ስምምነት መሠረትም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች የተግባር ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡
የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የዕቃዎች ጥገና እና ማስወገድ የመሳሰሉት ሥራዎች ከአርባ ምንጭ መካነ ኢየሱስ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ከሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካል ቤተ ሙከራ አስተባባሪ መ/ር ገላዬ ገረሱ ገልጸዋል፡፡
አሠልጣኝ መ/ር ዘለቀ ጊንቶ በበኩላቸው ሠልጣኞች በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን ዕውቀት በዩኒቨርሲቲው በተግባር ማየታቸውን ተናግረው በዩኒቨርሲቲው ለተግባር ትምህርት የተዘጋጀ 5 ኪ/ዋ ሶላር ሲስተም ያለ መሆኑ ሥልጠናውን በስኬት ለማካሄድና የተሻለ ዕውቀት ለመገብየት ረድቷል ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት