በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም መተዳደሪያ ደንብን በተመለከተ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ልዩ ረዳትና የአማካሪ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ እንደገለጹት የክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የመሆን ራእይ ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ከመማር ማስተማር ባሻገር በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በምርምር፣ በማማከናር በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ በክልሉ ብሎም በሀገራችን መንግሥት ከያዘው የልማትና የብልጽግና ራእይ አኳያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ፎረሙ በክልሉ ከሚገኙ 4 ዩኒቨርሲቲዎችና የ4 ኮሌጆች ጋር በ21017 ዓ/ም መመሥረቱን ያስታወሱት ዶ/ር ቦሻ ከምሥረታው በኋላ የመተዳደሪያ ደንብ ሰነድን በተመለከተ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በውይይቱም የሕግ ማዕቀፍ ሥራዎች፣ ያላለቁ ኤዲቶሪያል ሥራዎች፣ የፋይናንስ ጉዳዮች፣ የፎረሙ ቀጣይ የሥራ ሂደት፣ የዕለት ተዕለት ተግባራትን በኃላፊነት የሚሠራ ሴክሬቴሪያል ጽ/ቤት ማቋቋምና መሰል ጉዳዮች ላይ ሃሳብ መለዋወጣቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትና የፎረሙ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ፎረሙ ከተመሠረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የመተዳደሪያ ደንብ ሰነዱ ተዘጋጅቶ በሚገባ መታየቱን ገልጸው ለምዝገባ ዝግጁ በማድረግ ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ አቅርቦ ዕውቅናና ሕጋዊነት እንዲያገኝ ታልሞ ውይይቱ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ፎረሙ ሕጋዊነት ሲያገኝ የራሱ የሆነ አካውንት እንደሚኖረውና ከተለያዩ አጋር ተቋማትና ግብረ ሠናይ ድርጅቶች የሚሰበሰብ ገንዘብ በአካውንቱ ገቢ እንደሚሆን ዶ/ር አብደላ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ ሰነዱ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግና ሌሎች የሚታከሉ ጉዳዮች ላይ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በበኩላቸው በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እገዛ የሚፈልጉ ሥራዎችንና የልማት አጀንዳዎችን በመለየት መንግሥት የሚመድበውን ዉስን በጀት በመቆጠብ ሥራዎችን ሳይደጋገሙ ለመሥራት የሚስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ፎረሙ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ የመተዳደሪያ ደንብ ሰነዱም በተለያዩ የልማት ትኩረት መስኮች ላይ ሀገር በቀል ዕውቀትን በመለየትና በመቀናጀት የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሥራት የሚያስችሉ ዝርዝር ዓላማዎችን፣ ተግባራትን፣ የአባላትን የሥራ ድርሻና መዋቅራዊ አደረጃጀት በመለየት በተሟላ መልኩ የተደራጀ በመሆኑ ሕጋዊ ሰውነትን በማግኘት በተገቢው መንገድ ለመሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዮሐንስ ይትባረክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማር፣ ምርምር፣ ማኅበረሰብ ጉድኝትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገር ልማት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ በመሆኑ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ መንግሥት ጋር በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፎረሙን ሕጋዊ ለማድረግ ዓላማውንና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውን ያነሡት ዶ/ር ይትባረክ አባላቱ በየሦስት ወሩ አንድ ጊዜ ከኮሚቴው አባላት ጋር እየተገናኙ ሥራዎችን የሚገመግሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

