የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ከመማር ማስተማር ሂደት ጋር የተገናኘ ምርምር ማካሄድ የሚያስችል ‹‹Student Science›› የተሰኘ ጽንሰ ሃሳብ ተግባራዊ ሊያደረግ መሆኑን ጥቅምት 26/2017 ዓ/ም አሳውቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ጽንሰ ሃሳቡ ተግባር ተኮር የመማር ማስተማር ሂደት በመከተል ተማሪዎች ምርምርን በመለማመድ ዕውቀትና ልምዳቸውን የሚያዳብሩበት ቀላልና ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ በክፍል ውስጥና በቤተ ሙከራ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የመማር ማስተማር ሂደት ወደ ምርምር መቀየር እንደሚገባ አቅጣጫ የሚያሳይ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለጽንሰ ሃሳቡ ተግባራዊነት በትኩረት እንደሚሰራ ዶ/ር ዓለማየሁ አመላክተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና የጽንሰ ሃሳቡ አስተባባሪ Mr. Jan Dirk Dingemanse ምርምር በቂ ጊዜና የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች የሚስተዋሉበት መሆኑ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ሂደት በተግባርና በምርምር የታገዘ አለመሆኑ ጽንሰ ሃሳቡን ለመጠንሰስ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት ከመፍጠር አንጻር ለሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚሰጥ እንዲሁም ተማሪዎች ከሚወስዷቸው የትምህርት ኮርሶች ተያያዥነት ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመምረጥ አጫጭር ምርምሮችን በማከናወን ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
የሚትዮሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲ መምህር እስራኤል ገ/ሥላሴ እና የኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህር ፍሬው ደነቀ በበኩላቸው ጽንሰ ሃሳቡ ተለምዷዊ የምርምር አሠራርን በማስቀረት ከጊዜው ጋር የሚሄድ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎችን የሚያስተዋውቅ፣ ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በቀላሉ መፍታት የሚችሉበትን ስልት የሚያመላክት እንዲሁም የመምህራንና የተማሪዎችን የምርምር ዕውቀት የተሻለ እንዲሆን እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡
ጽንሰ ሃሳቡን በውኃ አቅርቦትና አካባቢ ምኅንድስና፣ ኤሌክትሪካል ምኅንድስና እና ሚትዮሮሎጂና ሃይድሮሎጂ ፋከልቲዎች፣ በባዮሎጅ ት/ክፍል እንዲሁም በማኅበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ሥር በሚገኙ ት/ክፍሎች ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት