የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተመራጭ የተማሪዎች ኅብረት ሥራ አመራር ከዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ጋር ጥቅምት 30/2017 ዓ/ም የትውውቅና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት መርሃ ግብሩ አዲሱ የተማሪዎች ኅብረት ሥራ አመራር ከዩኒቨርሲቲ አመራር አካላትና ከሌሎች የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ጋር ትውውቅ በማድረግ ሊከናወኑ በታቀዱ ተግባራት የጋራ ምክክር ማካሄድን ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ ፕሬዝደንቱ ኃላፊነት አገልጋይነት መሆኑን ጠቅሰው የተማሪዎች ኅብረት አመራሮች የተሰጣቸውን የኃላፊነት ዕድልና በዩኒቨርሲቲው የሚኖራቸውን የሕይወት ምዕራፍ በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ነባር የኅብረቱ ሥራ አመራር አካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና የሚገባው መሆኑንም ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ በበኩላቸው የትውውቅ መድረኩ ያልተለመደ እና በቀጣይም ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው ኅብረቱ ለዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ ተግባራት አጋዥ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የተቻለውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎኒያስ ፈንቴ የ2017 ዓ/ም የሥራ ዕቅድን አስመልክቶ እንደገለጸው ተማሪዎችን በተለያዩ ክበባት በማሳተፍ ክሂሎታቸውን እንዲገልጹ ማስቻል፣ የተማሪዎችን ሥነ ልቦናዊ ጫናዎች የሚቀንሱ ተግባራትን ማከናወን፣ ተማሪዎች ፈጣንና ተገቢ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሥርዓት ማመቻት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማስቀጠል በትኩረት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ከኅብረቱ ጎን በመሆን ለመሥራት ያሳዩት ተነሳሽነት ሊበረታታ የሚገባው ነው ያለው ተማሪ ሶፎኒያስ ተማሪዎች ዋና ዓላማቸው በሆነው ትምህርታቸው ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል፡፡
የኅብረቱ ዋና አፈ ጉባኤ ተማሪ ሶፎኒያስ መብራቱ እና የሁሉም ካምፓስ ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንቶች መርሃ ግብሩ ኅብረቱ በቀጣይ ማከናወን በሚገባው ጉዳዮች በኅብረቱ እና በዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሃይማኖት ማኅተመ ኅብረቱ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ገለጻ የሰጠ ሲሆን በኢንፎክን መጻሕፍት እና መረጃ ማዕከል አባላት የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ቀርበዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አካላት፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የሠላምና ደኅንነት አካላት እንዲሁም የሁሉም ካምፓስ የተማሪዎች ኅብረት ሥራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት