የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት 2ኛ ዙር ሀገራዊ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ የክረምት መርሐ ግብር የአቅም ማጎልበቻ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በመክፈቻ ንግግራቸው መንግሥት በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ እንዳለ ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ መምህራን ላይ መሥራት ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ለሁለተኛ ዙር መጀመሩን የገለጹት ዶ/ር ቦጋለ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራንና ርእሳነ መምህራን በሥልጠናው መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡ በትምህርቱ ይዘት ላይ የመምህራኑን አቅም ማጎልበት እንዲሁም በትምህርት አሰጣጥ ሥነ ዘዴና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ሥልጠናው እንደሚያተኩር ም/ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው ይህን መንግሥት የሰጠውን ትልቅ ኃላፊነት መምህራኑ በብቃት እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ለትምህርት ውድቀት የመምህራን ሚናቸውን አለመወጣትና በሚጠበቀው ልክ አለመሥራት እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸው የዘርፉን ምሁራን በማሠልጠንና አቅማቸውን በማሳደግ በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚቻል ታምኖበት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሥልጠናው መሰናዳቱን ተናግረዋል፡፡
በዳሰሳ ጥናት ልየታ በተደረገበትና መምህራን በሚያስተምሩበት ወቅት በበቂ ሁኔታ ለማስረዳት የሚከብዳቸው ክፍለ ትምህርት አተኩሮ ሥልጠናው እንደሚሰጥ ዲኑ ገልጸው ካለፈው ዓመት ሥልጠና በትምህርት ዓይነትና በሠልጣኙ ቁጥር ከፍ በማለት በ13 የትምህርት ዓይነት 3,270 ያህል መምህራን በሁለቱ ካምፓሶች እንደሚሠለጥኑ አቶ አንለይ ተናግረዋል፡፡ ይህም መምህራኑ በተገቢ ልምድ እንዲያስተምሩ ከማገዙም በላይ ተማሪው በተረዳው ልክ የመማር ፍላጎቱን በማሳደግ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አጋዥ እንደሚሆን ዲኑ አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ የሥልጠናውን ሂደት የተሳካ ለማድረግ በሚያስችሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት