አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና <<Czech Geological Survey (CGS)>> ከተሰኘ የምርምር ተቋም ጋር በመተባበር "Techniques of Quantifying Groundwater Resources" በተሰኘ ርእሰ ከጥር 25/2018 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የቆየ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
‹‹Techniques of Groundwater Resources, Challenges and Risk Management of Groundwater Sustainable Management of Water, Modern Drilling Techniques, Modeling and Remote Sensing Analysis of Groundwater›› የሚሉት ሥልጠናው ከተሰጠባቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተማነት መስፋፋት እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚታይበት በዚህ ወቅት ለመስኖ፣ ለኢንደስትሪ እና ለሥነ ምኅዳር መሻሻል ደኅንነቱ የተጠበቀ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ሀገሪቱ በስፋት የምትሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህንን የሀገር ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትብብር በመፍጠር እና አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ተሰሜ በበኩላቸው በኢንስቲትዩቱን ተመራማሪዎች የምርምር እና የኅትመት እንዲሁም ከሀገርና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው የተመራማሪዎችን በትብብር የመሥራት እንዲሁም በዘርፉ ያለውን ሳይንሳዊ ዕውቀት ከማሻሻል ባሻገር ለዘላቂ የውኃ ሀብት ልማት አጋዥ መሆኑን አክለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ ሥልጠናው "Improving Quality of Life" የተሰኘ በጋሞና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል የጂኦሎጂካል እና ሃይድሮሎጂ እንዲሁም የከርሰ ምድር ምኅዳር ላይ ያተኮረ የትብብር ፕሮጀክት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሳሙኤል አክለውም የከርሰ ምድር ውኃን በጥናትና ምርምር በመደገፍ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመረጃ ክፍተቶችን በማሻሻል እንዲሁም የከርሰ ምድር ውኃ አለኝታዎች ለመለየት እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያ ለመስጠት ወርክሾፑ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በ ‹‹Czech Geological Survey›› ተመራማሪ ፕሮፌሰር ክሪስቶፍ ቨርነር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትብብር በመፍጠር የኢትዮጵያን የጂኦሎጂ እና ሃይድሮሎጂ፣ የከርሰ ምድር ውኃ ተግዳሮቶች እና ዘላቂ የውኃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ መረጃ በማጠናቀር እና በቂ ጥናትና ምርምር ሲሠራ የቆየ መሆኑና በዚህም በርካታ ዓለም አቀፍ የምርምር እና የኅትመት ሥራ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር የመሥራት አቅሙ ጠንካራ መሆኑንና በዚህም በትምህርት ልማት እንዲሁም በምርምርና በኅትመት መስክ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሥልጠናው ከአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩትና ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተወጣጡ መምህራንና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከሲዳማ ክልልና ከጋሞና ጎፋ ዞኖች የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት





