አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጨንቻ እና ዲታ ወረዳዎች የአካባቢውን የአየር ንብረት እና አግሮ ኢኮሎጂ መሠረት ያደረገ የተሻሻሉ የባሸካላ ዝርያዎች የማላመድ (adaptation trial) ምርምር በተሳካ ሁኔታ አከናውኗል፡፡ በጋሞ ደጋማ አካባቢዎች የተለመደው የአካባቢ የባሽካላ ዝርያ በማሳ ላይ ከ7-9 ወራት የሚቆይ በመሆኑ፣ ለሌሎች ተተኪ ሰብሎች ዕድል ባለመስጠቱና ከዚህ ሁሉ ቆይታ በኋላም ከሰብሉ የሚገኘው ምርት በጣም ዝቀተኛ በመሆኑ ለዘመናት ለአርሶ አደሮች ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ይህንን ችግር ለመፍታት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከባኮ፣ ቁሉምሳ እና አዴት ግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙ አሥር የተሻሻሉ እና ሁለት የአካባቢ ዝርያዎችን በድምሩ አሥራ ሁለት ዝርያዎችን በጨንቻ እና ዲታ ወረዳዎች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የማላመድ ምርምር (adaptation trial) ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ከተሞከሩት ዝርያዎች መካከል አራት የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአካባቢው እና ተመሳሳይ የአየር ንብረት ላላቸው የጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ተስማሚ፣ ምርታማ እና ፈጥነው የሚደርሱ መሆናቸው በምርመሩ ውጤት ተረጋግጧል፡፡
የተመረጡትን ዝርያዎች የዘር ጥራት ጠብቆ ለማቆየት (seed maintenance) እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ የዘር ማባዛት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ይህ ተግባር የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከሙከራ ደረጃ (research phase) ወደ ስፋት ስርጭት (scaling up) ለማሸጋገር የሚያግዝ አስፈላጊ ተግባር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት የተመረጡ ዝርያዎች በመስክ ሁኔታ ያላቸውን ምርታማነት፣ በአጭር ጊዜ የመድረስ ባሕርይ እና ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚነት በተግባር ለማሳየትና ለማስተዋወቅ በጨንቻ ካሌ ጎቶራ ቀበሌ በተመረጡ አርሶ አደሮች ማሳ እና በጨንቻ ማረሚያ ተቋም የተዘጋጁ የሠርቶ ማሳያ ቦታዎች ላይ ዝርያዎቹ ተዘርተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው የመስክ ጉብኝት ጥር 13/2018 ዓ/ም የተካሄደ ሲሆን የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ከጋሞ ዞን፣ ከጨንቻና ከዲታ ወረዳዎች እና ከጨንቻ ከተማ የመጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ሞዴል አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተሰጡት ዋና ዓላማዎች አንዱ በሆነው የምርምር ዘርፍ በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ከመደገፍና ሀገራችን የምትከተለውን በምግብ ራስን መቻል ዕቅድ ለማሳካት በምርምር የሚገኙ ምርጥ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በባሽካላ ላይ የተደረገው ምርምር የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በጥቂት መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኝ በማድረግ በተጨባጭ የአካባቢውን አርሶ አደር ችግር የሚፈታ መሆኑን ተናግረው ሥራውን በሰፊው ለመሥራት ዩኒቨርሲቲው ለተመራማሪዎቹም ሆነ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርገል ብለዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሁለተኛው የትኩረት መስኩ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በምርምር የተደገፉ የአካባቢውን አርሶ አደርም ሆነ እንደ ሀገር ዘርፉን የሚደግፉ የምርምር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡ የባሽካላ ሰብልን አስመልክቶ የተደረገው ምርምርም ሆነ በመስክ ምልከታው የታየው ውጤት እጅግ አስደሻች ነው ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በቀጣይ በተሻለ በጀት ብዙኃኑን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ እና ሌሎችም የጋሞ ከፍተኛ ቦታዎች ከፍተኛ የሆነ የእርሻ መሬት ጥበት ያለባቸውና አፈሩ አሲዳማ መሆኑን ጠቁመው ምርምሩ ይህን ችግር በመቅረፍ ለአርሶ አደሩ ሁነኛ መፍትሔ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ በአነስተኛ በጀት የተሠራ ቢሆንም የታየው ውጤት አስደሳችና በቀጣይ ሰፊ ሥራዎችን የሚፈልግ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እንደሚሠራበትም ገልጸዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ዲንና የምርምሩ ተባባሪ ተመራማሪ ዶ/ር ደግፌ አሰፋ በኮሌጁ የግብርናውን ዘርፍ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚደግፉ በርካታ ምርምሮችና ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው ከምርምሮቹ አንዱ በሆነው የባሽካላ ዝርያዎች ምርመር የታየው ውጤት አስደሳች ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ይህንን በማስፋት በዩኒቨርሲቲው በግርጫ ምርምር ማእከል ማሳ በሰፊው ለመዝራት ብሎም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለአርሶ አደሩ በሰፊው ለማሰራጨት ይሠራል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ የዕፅዋት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርትና የምርምሩ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር መሠረት ፋንታ ነባሩ የአካባቢ ባሽካላ ዝርያ በማሳ ላይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ከመሆኑም በላይ ምርቱ በጣም ዝቅተኛና በበሽታ በቀላሉ የሚጠቃ መሆኑን እንዲሁም የተሻሻሉ የባሽካላ ዝርያዎች በአካባቢው እስካሁን ያልተሞከሩ በመሆኑ አርሶ አደሩ የአካባቢውን ዝርያ (local cultivar) ከመዝራት ውጭ አማራጭ እንዳልነበረው ማየታቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች ወደ አካባቢው አምጥተው ለመሞከር የመነሻ ሃሳብ እንደሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ እንደ ተመራማሪዋ ማብራሪያ በዚህ ምርምር የተመረጡት ዝርያዎች ከአራት እስከ አምስት ወራት ውስጥ የሚደርሱ ሲሆን በሔክታር በአማካይ እስከ 60 ኩንታል የሚደርስ ምርት ማስመዝገባቸው ታይቷል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ዝርያዎች የአካባቢው አሲዳማ መሬት ሳይበግራቸው በተለይ ዋግና ሌሎችም በሽታዎችን ተቋቁመው አመርቂ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ተመራማሪዋ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ይህ የምርምር ውጤት ሰፊውን የጋሞ ደጋማ አካባቢዎች የባሽካላ አምራች ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ የምግብ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ አስረድተዋል፡፡
በምርምሩ በተለዩት አራቱ የባሸካላ ዝርያዎች የማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ምርምሯን የሠራችው የዩኒቨርሲቲው የአግሮኖሚ ማስተርስ ተማሪ ቦጋለች ቦራ የባሽካላ ሰብል በጨንቻ አካባቢ በሰፊው የሚመረትና በአርሶ አደሩ ዘንድ ተመራጭ ቢሆንም የረዥም ጊዜ የማሳ ላይ ቆይታውንና የአርሶ አደሩን ልፋት የማይመጥን አነስተኛ ምርት መፍትሔ ሳያገኝ መቆየቱን ትገልጻለች፡፡ አሁን ላይ እነዚህ ውጤታማ ዝርያዎች በዩኒቨርሲቲው መምጣታቸው መፍትሔ ሳያገኝ የቆየውን የባሽካላ ችግር እንደሚፈታና በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚገጥመውን ብክነት ጭምር የሚያስቀር መሆኑን አብራርታለች፡፡ በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለው አቀባበል አስደሳችና ለቀጣይ ሥራዎች የሚየነሣሣ መሆኑንም ገልጻለች፡፡
በመስክ ምልከታው የታደሙ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምንም እንኳ ባሽካላ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ተወዳጅ ሰብላቸው ቢሆንም የማሳ ላይ ቆይታው ለሌሎች ሰብሎች ዕድል የማይሰጥ ብሎም ምርቱ ደርሶ ሲወቃ ፍሬውን ከገለባው መለየቱ እጅግ ጉልበት የሚጠይቅ ፈታኝ ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያስተዋወቃቸው የባሽካላ ዘርያዎች በአጭር ጊዜ ደርሶ ከነባሩ የተሻለ ምርት የሚሰጥ መሆኑን በማየታችን ተደስተናል ያሉት አርሶ አደሮቹ በየማሳዎቻችን ዘርተን ለመጠም ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ከሠርቶ ማሳያ ቦታዎቹ መካከል አንዱ የጨንቻ ማረሚያ ተቋም በመሆኑ ከጋሞ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ታራሚዎች በሠርቶ ማሳያው ወቅት የተመረጡ ዝርያዎችን አግባብነት በተግባር በመረዳታቸው ከተቋሙ ሲወጡ ያገኙትን ተግባራዊ ልምድና የተመረጡ ዝርያዎችን ወደ የመጡባቸው አካባቢዎች በመውሰድ ለማስፋፋትና ለማሰራጨት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ተጠቅሷል፡፡
በሠርቶ ማሳያው መስክ ምልከታ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ዩኒቨርሲቲው ያቀረበውን የባሽካላ ምርምር ውጤት በከፍተኛ አድናቆት እንደተቀበሉት ገልጸዋል፡፡ ባለድርሻ አካላቱም ይህ የምርምር ውጤት ለአካባቢው አርሶ አደር ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ የተመረጡትን ዝርያዎች የዘር ብዜት በማከናወን ለመላው አርሶ አደር እንዲደርሱ ለማሰራጨት እንዲሁም ወደ ሌሎች የጋሞ ደጋማ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ኃላፊነት ወስደው በትጋት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት




