በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች በቡድን ሥልጠና ፕሮግራም (Team Training Program/TTP) በተለያዩ የጤናና የትምህርት ተቋማት ላይ ያሠሯቸውን ፕሮጀክቶች ታኅሣሥ 25/2017 ዓ.ም አስመርቀዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ፕሮጀክቶቹ በአርባ ምንጭ ልማት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በሲቀላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እና በሼቻ ጤና ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሠሩ ሲሆን የእጅ መታጠቢያ የውኃ ቦኖ እና ለሴት ተማሪዎች ማማከሪያና ማረፊያ ክፍሎች ግንባታ እንዲሁም የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ ሞዴስና የደም ግፊትና የስኳር መጠን መለኪያ መሣሪያ ድጋፎችን ያካትታሉ፡፡
የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተር አቶ በላይ ቦዳ ችግሮችን መለየትና መፍትሔ ሠርቶ ማሳየት የTTP ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቁመው የተሠሩት ሥራዎች ረዥም ጊዜ መቆየት እንዲችሉ ጥበቃና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለተቋማት ኃላፊዎች አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይ ጤናን የሚመለከቱ አስፈላጊ ሙያዊና ቁሳዊ ድጋፎችን ለማድረግ እንደ ኮሌጅ ፈቃደኝነታቸውን አመላክተው ፕሮጀክቶቹን ለሠሩት የቡድኑ አባላትና ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ መ/ርት ገሊላ ቢረሳው ከተለያዩ 5 የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ ተመራቂ ተማሪዎች የተቋማቱን ችግር የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን ሠርተው ለምረቃ ማብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቡድን ሥልጠና ፕሮግራም ችግሮችን ለይቶ መፍትሔ የማምጣት፣ በቡድን የመሥራት ባህልን፣ የመሪነት ልምድንና ማኅበራዊ ትስስርን ለማዳበር እንደሚረዳቸው ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹TTP›› በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ የቀረበና የትምህርታቸው አንዱ አካል መሆኑን የጠቆሙት መ/ርት ገሊላ በተግባር የማኅበረሰቡን ችግር መፍታታቸው ሲረጋገጥ የትምህርት ውጤት እንደሚሰጣቸውና የመመረቂያ አንዱ መስፈርት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሲቀላ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ዋና ርዕሰ መምህር አርጋቸው አሻ እና የአርባ ምንጭ ልማት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መ/ር ፍቃዱ ታደሰ በት/ቤቶቹ ያሉ ችግሮችን በመለየት ድጋፉ መደረጉን ገልጸው ሴት ተማሪዎቻችን የተለያዩ የጤና እክሎች ሲያጋጥማቸው የሚያርፉበት ክፍል መሠራቱና የንጽሕና መጠበቂያ ድጋፉ ሴቶችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡
በፕሮጀክት ሥራው ዋና አስተባባሪ ተመራቂ ተማሪ ባንታየሁ ካስትሮ እና ያዕቆብ መሸሻ ከመንግሥት፣ ከግል ተቋማትና ከግለሰቦች በተሰባሰበ ገንዘብ እንዲሁም ሎተሪዎችን አዙሮ በመሸጥ በተገኘ ገቢ ፕሮጀክቶቹን ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በወዜ ጤና ጣቢያ ላይ በነበሩ ቡድኖች ነጻ ሙያዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት