ዶ/ር ገናዬ ፀጋዬ የሕትመት፣ ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኑ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዋ ሴት ዶክተር የሆኑት ዶ/ር ገናዬ ፀጋዬ በዩኒቨርሲቲው አዲስ የተቋቋመው የምርምር ሥራዎች ህትመት፣ ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡

በሆለታ ከተማ ተወልደው ያደጉት ዶ/ር ገናዬ ፀጋዬ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሆለታ የተከታተሉ ሲሆን የመሰናዶ ትምህርታቸውን በአምቦ ተከታትለዋል፡፡ ዶ/ር ገናዬ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ 2ኛ ዲግሪያቸውን ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በአፈርና ውኃ ጥበቃ ምህንድስና እንዲሁም የዶክተሬት ዲግሪያቸውን ቤልጂየም ከሚገኘው KU Leuven  ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሕይወት ሳይንስ ምህንድስና አግኝተዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በ2004 እንደተቀላቀሉ የተናገሩት ዶ/ር ገናዬ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከመምህርነት ባሻገር በትምህርት ከፍል ኃላፊነትና በተለያዩ የምርምር ሥራዎችና ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ዩኒቨርሲቲውን እያገለገሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ገናዬ በዳይሬክተርነት የሚመሩት የህትመት፣ ስነዳና ስርጭት ዳይሬክቶሬት በዋናነት ከዚህ ቀደም ተግባሩ በምርምር ዳይሬክቶሬት ሥር ሲፈፀም እንደ ነበር አስታውሰው ስራው ራሱን በቻለ ዳይሬክቶሬት ቢመራ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል በመታመኑ በዳይሬክቶሬት ደረጃ እንደ ተቋቋመ ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በአንድ ጽ/ቤትና በሁለት ቦርዶች የተዋቀረ ሲሆን እነሱም የህትመት፣ ስነዳና ስርጭት ጽ/ቤት፣ ጆርናል ኤዲቶሪያል ቦርድ እና ሪሰርች ኢቲክስና ኢንቴግሪቲ ኤዲቶሪያል ቦርድ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ ወጥ የሆኑ የሳይንሳዊ ህትመቶች መገምገሚያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች የሚሰሩ የተለያዩ ጥራታቸውን የጠበቁ የምርምር ሥራዎች በታወቁ  አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ በማሳተም የመሰነድና የማሰራጨት ሥራ እንደሚያከናውን ዶ/ር ገናዬ ገልፀዋል፡፡
ሳይንሰዊ መርሆችን የተከተሉ የምርምር ውጤቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በቁጥርም ከፍ ብለው መታተማቸው ዩኒቨርሲቲው በሳይንሱ ዓለም ታዋቂ፣ ተወዳዳሪ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውን የምርምር ተቋም ከማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ያሉት ዶ/ር ገናዬ ከዩኒቨርሲቲው አልፎ ለተመራማሪዎችም አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያስገኝላቸዋል ብለዋል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ሳይንሰዊ የምርምር ውጤቶች  በምርምር ጆርናሎች እንዲታተሙ ድጋፍና ማበረታቻ የሚያደርግ በመሆኑ ተመራማሪዎች ከሳቸው ቢሮ ጋር በጋራ በመስራት ራሳቸውንም ሆነ ዩኒቨርሲቲያቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የ3ኛ ዲግሪ መመረቂያ ሥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና በዓሳ ምርት በሚታወቀው ጫሞ ሐይቅ ዙሪያ ባሉ ችግሮች ላይ በማተኮር እንደሰሩ የሚናገሩት ዶ/ር ገናዬ በዋናነት ጥናታቸው በፓርኩ ሀብት ተጠቃሚዎችና የተፈጥሮ ሀብቱ ጠባቂ የመንግስት አካላት መካከል ያለውን ግንኙነትና መስተጋብር ነባራዊ ሁኔታ፣ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል መኖር ስላለበት መስተጋብርና ግንኙነት አስመልክቶ በፓርኩ ላለፉት 30 ዓመታት በላይ ሲተገበር የኖረው ዘዴ ማህበረሰቡን አግላይ ወይም ከላይ ወደ ታች የሚባለው የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቂያ ዘዴ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ገናዬ የምርምር ግኝት መሠረት ላለፉት ዓመታት ሲተገበር በነበረው ዘዴ ፓርኩ ከአደጋ ሊጠበቅ ካለመቻሉም ባሻገር የፓርኩን ሀብት ተጠቃሚዎችም በቂ አገልግሎት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ዘዴው አግላይና ግለሰቦችን ያላሳተፈ በመሆኑ በፓርኩ ውስጥም ሆነ ውጪ የሚኖሩ ሰዎች ለፓርኩ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ አሁን ላይ ፓርኩንም ሆነ ሐይቁን ከአደጋ ለመታደግ መከተል ያለብን ዘዴ ከዕቅድ ጀምሮ አስከ ትግበራ ማህበረሰቡን ያሳተፈ፣ ያሳመነና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ዘዴ መመረጥ እንዳለበት አቅጣጫ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በነበሩ ዘዴዎች ማህበረሰቡን ያላሳተፈ  ውሳኔ እየተላለፈ የሚቀጥል ከሆነ የፓርኩ ህልውና ላይ  አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
የጥናት ውጤታቸውን ለመተግበር ከዩኒቨርሲቲው IUC ፕሮግራም፣ GIZ ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንዲሁም ከፓርኩ ጋር በጋራ በሚሰራው ሥራ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ገናዬ አሁን ላይ እየመሩ የሚገኙትን አዲስ ቢሮ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙና ለመከታተል ላሰቡ ሴት  መምህራን ልምድና ተሞክሮዋቸውን በማካፈል ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ለሳቸው እዚህ ቦታ መድረስ ድጋፍ ላደረጉ ቤተሰቦቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውና በውጪና በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የጥናት አማካሪዎቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት