አርባ ምንጭና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም መስኮች በቅንጅትና በትብብር እንደሚሰሩ የሁለቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቶችና ሌሎች አመራሮች ተናገሩ፡፡Click here to see the pictures

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፐሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ ዩኒቨርሲቲያቸው ከተመሠረተ 3ኛ ዓመቱን መያዙን ገልፀው ዩኒቨርሲቲያቸው አዲስ እንደመሆኑ በርካታ ክፈተቶችና ጉድለቶች ያሉበት በመሆኑ እነዚህን ጉድለቶች ለመሙላት በምናደርገው ጥረት ውስጥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቁሳቁስ፣ የሰው ኃይል ድጋፍና አቅም ግንባታ ላይ፣ ልምድ በማካፈል እንዲሁም የቤተ-ሙከራ የተግባር ትምህርቶችን ለተማሪዎቻችን በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልን ነው ብለዋል፡፡ ካልተደጋገፍንና ካልተባበርን የተሰጠንን ሀገራዊ ተልዕኮ ማሳካት አንችልም ያሉት ፕሮፌሰሩ ከዚህ አንፃር በሁሉም መስኮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጀመርነውን መልካም ግንኙነትና ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መከፈት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ሁኔታ የሥራ ጫናን የሚቀንስ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው በቆየባቸው 3 ዓመታት እንደ ነባር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ድጋፎችን ለዩኒቨርሲቲው ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ለዩኒቨርሲቲው የሚደረገው  ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዳምጠው የማኅበረሰቡን ሕይወት መቀየር የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተልዕኮ እንደመሆኑ በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በጋራና በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል፡፡
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ አባልና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሥራ ከጀመረ 3 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመዋቅርና መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት አንፃር ለውጦችን እያሳየ ነው፡፡ ተቋማት ለብቻቸው ከሚሮጡ በጋራና በትብብር ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ላይ መድረስ ይችላሉ ያሉት ዶ/ር የቻለ አንዱ የአንዱን ክፍተት እየሞላ ሁለቱ ተቋማት በሁሉም መስኮች በትብብር ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በግላቸው እንደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባልና እንደ አ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራር የሁለቱ ተቋማት ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ም/አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ደፋሩ በበኩላቸው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የደቡብ ኦሞ ሕዝብ ባለውለታ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በዋናነት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ነፃ የትምህርት ዕድሎችን በመስጠት በዞናችን በመምህርነትና በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሠሩ ምሁራንና ባለሞያዎችን በማሰልጠን የዋለው ውለታ የሚረሳ አይደለም ብለዋል፡፡ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የዩኒቨርሲቲዎች ሚና የማይተካ መሆኑን የተናገሩት ም/አስተዳዳሪው ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል የሚረዱ ምርምሮችንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ከመሥራት ረገድ በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡ በተለይ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተቋም እንደመሆኑ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እንዲቀጥል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላለፈው እስካሁን ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍም በዞኑ አስተዳደርና ሕዝብ ስም መስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት