አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ‹AMU-IUC› ፕሮግራም 2ኛ ዙር የትብብር ቆይታ ጊዜ አገኘ

በሥሩ 6 ፕሮጀክቶችን ይዞ ላለፉት 5 ዓመታት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና አካባቢው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየው IUC ፕሮግራም በገለልተኛ አካላት በተደረገ የአፈፃፀም ግምገማ የላቀ ውጤት በማስመዝገቡ የ2ኛ ዙር የ5 ዓመት ዕድል ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

የፕሮግራሙ ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለጹት IUC ፕሮግራም በሁለት ዙር የተከፈለ የ10 ዓመት ቆይታ ያለው ሲሆን 2ኛው ዙር ዕድል የሚወሰነው በመጀመሪያው ዙር በሚመዘገበው ውጤት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ላለፉት ዓመታት የተማሪዎችን ውጤታማነት፣ የፋይናንስና የአፈፃፀም ሪፖርቶችንና ሌሎችም ሥራዎችን በለጋሽ አካሉ ተመርጦ የመጣው ገለልተኛ ገምጋሚ ቡድን በአካል በመገኘት ባደረገው የአፈፃፀም ግምገማ ፕሮግራሙ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ በመቻሉ 2ኛ ዙር ዕድል ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ፕሮግራሙ በዩኒቨርሲቲው በነበረው ቆይታ 19 መምህራን ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ቤልጂየም ሀገር በሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች መማር መቻላቸው፣ በየ15 ደቂቃው ዳታ ማቀበል የሚችል ዘመናዊ የሐይቅ የውሃ ጥራት መለኪያ መሳሪያና የአውቶማቲክ የአየር ሁኔታ ጣቢያዎችንና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ-ሙከራዎችን በዩኒቨርሲቲው ማቋቋም መቻሉ፣ የዩኒቨርሲቲውን የICT መሠረተ ልማት ከማጎልበት አንፃር በጫሞ ካምፓስ የተገነባውን Data Miror ማዕከል ጨምሮ በዘርፉ የተሠሩ ሌሎች ሥራዎች፣ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክንና ጫሞ ሐይቅን ለመታደግ እየተሠሩ ያሉ የአቅም ግንባታና የተግባር ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ረ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው እየተገባደደ ያለው የIUC ፕሮግራም በመጀመሪያው የትብብር ዘመን ለዩኒቨርሲቲው በርካታ ጥቅሞችን ማስገኘቱን ገልጸው የተማሪዎች የምርምር ግኝቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ የኅትመት ጆርናሎች ላይ መታተማቸውና የምርምር ውጤቶቹ ለሀገራዊ ችግሮች መፍቻ ግብዓት መሆን መጀመራቸው፣ በተለያዩ ዘርፎች ተጨማሪ የመምህራንና የቴክኒክ ረዳቶችን አቅም ግንባታ የአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን እዚሁና ቤልጂየም ሀገር ሄደው እንዲወስዱ መደረጉ፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የመምራት፣ የመከታተልና በተያዘለት ፕሮግራም ጊዜ የማጠናቀቅ ተሞክሮ መገኘቱ በፕሮግራሙ ከተገኙ ጠቀሜታዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።

እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲያችን 2ኛውን ዙር የትብብር ዕድል ማግኘቱ ተጨማሪ የPhD ትምህርት ዕድል የሚያገኙ መምህራን ቁጥር እንዲጨምርና ዩኒቨርሲቲው የዳበረ የሳይንስ ዕውቀትና ክሂሎት የሚያስተዋውቁ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንዲኖሩት እንሚያደርግ እንዲሁም ለየዘርፉ የሚሆኑ ሀገራዊ የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ ሀሳቦች አበርክቶት ላይ የሚኖረውን ተሳትፎ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ሀገርና እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለተቀረፀው የ10 ዓመት የመምህራን ልማት ዕቅድ መሳካት ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲውን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትና ገጽታ ግንባታን ያሳድጋል ብለዋል።

ለፕሮግራሙ የመጀመሪያው የሥራ ዘመን ውጤታማነት የበኩላቸውን ለተወጡት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ለሁሉም የአሁንና የቀድሞ ም/ፕሬዝደንቶች፣ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ለነበሩት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንዲሁም በትብብር ሲሠሩ ለነበሩ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ክፍሎች ሁሉ የፕሮግራሙ ኃላፊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት