የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም የ2 ዓመታት ዞናዊ አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሄደ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም የ2 ዓመታት ዞናዊ አፈፃፀሙ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት የካቲት 16/2013 ዓ/ም ወርክሾፕ አዘጋጅቷል፡፡ ፕሮግራሙ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት የቀሩት በመሆኑ መልካም ተሞክሮዎችን በዘላቂነት ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላቱ የሚጠበቁ ሥራዎችና ኃላፊነቶች በመድረኩ በሰፊው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ2019 እና 2020 የሠርቶ ማሳያና የቅድመ ማስፋፊያ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ ሲሆን የቆይታ ጊዜው ሊጠናቀቅ በመሆኑ በ2 ዓመታት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው የተሠሩ ሥራዎችን፣ መልካም ተሞክሮዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመቃኘት ጅምር ሥራዎችን በተለያዩ ተቋማት በባለቤትነት አውርዶ ለመሥራት በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት ወርክሾፑ ተዘጋጅቷል፡፡

የፕሮግራሙ የማስፋፊያ ባለሙያ አቶ ሰሎሞን ይግረም የአፈፃፀም ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አርባ ምንጭ ክላስተር በጋሞና ጎፋ ዞኖች በደራሼ፣ ም/ዓባያ፣ ዛላና ቁጫ ወረዳዎች 16 ቀበሌያት የግብርና ምርታማነት የሚጨምሩ ተሞክሮዎችን በማልማትና በማላመድ፣ የተሻሻሉና የአርሶ አደሩ ምርጫ የሆኑ ምርጥ ዘሮች እንዲቀርቡ እገዛ በማድረግ እንዲሁም የማኅበረሰቡንና የተቋትን አቅም በሥልጠናና ሌሎችም መንገዶች በመገንባት ባለፉት 2 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

ፕሮግራሙ እስከ አሁን በነበረው ቆይታ በ4ቱ ወረዳዎች 6,697 የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችና 16,835 ሌሎች በድምሩ 23,560 አርሶ አደሮችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተደራሽ አድርጓል፡፡ የበቆሎ፣ ማሽላ፣ ድቡልቡል ድንች፣ ፓፓያ፣ ብርትኳንማ ቀለም ያለው ስኳር ድንች እና የጓሮ አትክልት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያ አቅርበው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ከፍ እንዲል ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም 5,809 አርሶ አደሮች በቀጥታና 12,423 አርሶ አደሮች በተዘዋዋሪ በድምሩ 18,232 አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

አቅም ግንባታን በተመለከተ 6,697 አርሶ አደሮችና 44 ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠናዎችን አግኝተዋል፡፡ በግብርና ሥራ ላይ የሴቶችን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ አድካሚ ባህላዊ አሠራሮችን የሚያስቀሩ 30 የእንሰት መፋቂያና 400 የበቆሎ መፈልፈያዎችን ለሴት አርሶ አደሮች አጠቃቀሙን በማሠልጠን ለማዳረስ ተችሏል፡፡

የዝናብ ወቅትና መጠን መዋዠቅ፣ የዘር እጥረት በአንዳንድ የጓሮ አትክልቶች የተባይ መከሰት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት፣ በአንዳንድ ቀበሌያት የአርሶ አደሮች ግጭቶችና ሀገር አቀፍ የፀጥታ ሁኔታዎች በፕሮግራሙ ቆይታ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም በ4ቱ ወረዳዎች ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክት መቆየቱን ጠቅሰው ፕሮግራሙ በወረዳና ቀበሌያት ደረጃ ጠንካራ አደረጃጀቶችን የፈጠረ በመሆኑ ሥራዎችን ለማስቀጠል የሚያዳግት አይደለም ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

በወርክሾፑ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ቤኔፊት ሪያላይዝ ጋር በመሥራታቸው ያገኟቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችና ላጋጠሟቸው ችግሮች የወሰዱትን የመፍትሄ እርምጃ የየአካባቢያቸውን ተሞክሮ ለአብነት በመጥቀስ አሳይተዋል፡፡ ፕሮግራሙ ቀጣይነት ባይኖረውም እስከ አሁን በተፈጠረላቸው አቅም አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው የወረዳ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በጋራ መሥራት የሚችሉ በመሆኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኒክ፣ የባለሙያና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወርክሾፑ የጋሞና ጎፋ ዞኖች የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የደራሼ፣ ም/ዓባያ፣ ዛላና ቁጫ ወረዳዎች የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሰብል ልማት ባለሙያዎች፣ የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊዎችና የቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም ተጠሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት